በዓላት ሲከበሩ የተቸገሩትን በመደገፍ ሊሆን ይገባል- አቶ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የጥምቀትንም ሆነ ሌሎች በዓላቶችን ስናከብር በተለያየ ምክንያት የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ሊሆን እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳደሩ በጎንደር ከተማ አፄ ፋሲል ጥምቀተ ባህር በተካሄደው ስነ ስርዓት ላይ እንደገለጹት የጥምቀት በዓል ከባህላዊ ክዋኔው ባለፈ የኢትዮጵያ መገለጫ እየሆነ ነው።
“የዘድሮውን በዓል ስናከብር ባላፈው ዓመት በዚሁ ጥምቀተ ባህር በደረሰ ድንገተኛ አደጋ የተሰውትን፣ በህግ ማስከበር ህይወታቸው ያለፈና በማንነታቸው የተሰውትን ወገኖች በማሰብ ነው” ብለዋል።
እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመደግፍና በማገዝ አጋርነትን በማሳየት ሊሆን እንደሚገባ አመልክተው ወቅቱ ጠንክራ መተጋገዝና መተሳሰብ የሚጠይቅ ጊዜ እንደሆነ ጠቁመው “ይህን አስቸጋሪ ወቅት ለመሻገር ትብብር ወሳኝ ነው” ሲሉ ገልፀዋል።
“በጎንደር ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘቱን በጠበቀ አግባብ እየተከናወነ ያለው የጥምቀት በዓል በመላው አለም የበለጠ እውቅና እንዲኖረው በትኩረት ይሰራል” ብለዋል።
የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ በበኩላቸው የጥምቀት በዓል ለጎንደርና አካባቢው ህዝብ የማንነቱ መገለጫ ታሪካዊ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
“የጥምቅት በዓል መለያየትን በአንድነት፣ ጥልን በፍቅር የሚያስተምርና ወደ ከፍታው እንድንወጣ ትምህርት የሚወሰድበት በዓል ነው ” ሲሉም ተናግረዋል።
“ከተማዋ ጥንታዊ ታሪኳን ጠብቃ እንድትቀጥልና በኢኮኖሚ ጠንካራ እንድትሆን የሁሉም ትብብር ይጠይቃል” ሲሉ ከንቲባው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!