የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የከተራና የጥምቀት በዓል በሠላም መጠናቀቁን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የከተራና የጥምቀት በዓል በሠላም መጠናቀቁን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እና ህብረተሰቡን አጋዥ በማድረግ ባከናወነው ተግባር የከተራ እና የጥምቀት በዓላት በሰላም መጠናቀቃቸውን ነው የገለፀው፡፡
ለዚህም ህብረተሰቡ ለበዓሉ በሠላም መጠናቀቅ ላበረከተው አስተዋፅኦ ኮሚሽኑ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
እንዲሁም በከተራውም ሆነ በበዓለ ጥምቀቱ ዕለት የታየው የወጣቱ ሰላም እና ፀጥታን የማረጋገጥ ፍላጎት እና ተነሳሽነት በሌሎች መደበኛ የፀጥታ ማስከበር ስራዎች ላይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኮሚሽኑ ጠይቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በከተራ እና በጥምቀት በዓላት ላይ የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች ከነ ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡
በከተራ እና በበዓሉ ዕለት በነበረው የፀበል መርጨት ስነ ስርዓት ወቅት የነበረውን ግፊያ እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም አምስት የስርቆት እና አንድ የቅሚያ ወንጀል ተፈፅሟል፡፡
እንዲሁም አንድ ግለሰብ አደንዛዥ ዕፅ ይዞ ሲንቀሳቀስ በፍተሻ ተገኝቷል፡፡
በአጠቃላይ ወንጀሎቹን ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ 7 ግለሰቦች ተይዘው ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን አምስት የተሰረቁ ሞባይል ስልኮችም በተጠርጣሪዎቹ እጅ መገኘታቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!