የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሬድዋን ከተመድ የሴፊቲና ሴኪዩሪቲ አንደር ሴክሬታሪ ጄኔራል ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴፊቲና ሴኪዩሪቲ አንደር ሴክሬታሪ ጄኔራል ጊሌስ መቻዱን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ስለ ትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ፣ በክልሉ የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ የሚደረገው ርብርብ፣ የመልሶ ማቋቋም ሥራ፣ የህወሃት ጁንታ ያፈራረሳቸው መሰረተ ልማቶች መልሶ ግንባታ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የመንግሥት መዋቅርን መልሶ ለማደራጀት እያከናወነ ያለው ስራና ያጋጠሙ ችግሮች ተዳሰዋል።
በትግራይ ክልል ያሉ የኤርትራ ስደተኞች ሁኔታ፤ እንዲሁም በትግራይ ክልል እንቅስቃሴ ከማድረግ አንፃር በለጋሽ ድርጅቶችና ሌሎች አካላት የሚነሱ ጥያቄዎችም ላይ መክረዋል።
አቶ ሬድዋን በትግራይ ክልል የተደረገው የህግ የበላይነት ማስከበር ዘመቻ “የህወሃት ጁንታ ቡድን በእብሪት ተነሳስቶ በአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመፈፀሙ ምክንያት የተደረገ የአገር ህልውና ለመታደግ የተደረገ ነው” ብለዋል።
የህወሃት ቡድንና ቡድኑ የሚተማመንባቸው አይዞ ባይ ኃይሎች፣ ቡድኑ በሶስት ሳምንታት ዘመቻ ተፍረክርኮ መበተን ብሎም መሸነፍ ከባድ ድንጋጠ ስለፈጠረባቸው በተለያየ ሁኔታ ትኩረት ለማግኘት የሚደረግ መፍጨርጨር በመኖሩ በክልሉ የሚደረግን እንቅስቃሴ በጥንቃቄ እንዲደረግ ሆኗል ነው ያሉት።
በክልሉ የሰብአዊ ድጋፍ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ለሚያደርጉት አስፈላጊ የሆነ እንቅስቃሴ ጥንቃቄ ሳይዘነጋ መንግሥት እገዛና ትብብር እያደረገላው ከመንግሥት ጋር ተባብረው የሰብአዊ ድጋፍን በክልሉ እያቀረቡ መሆኑንም ገልፀዋል።
የተመድ የሴፊቲና ሴኪዩሪት አንደር ሴክረታሪ ጄኔራል ጊሌስ መቻዱን በበኩላቸው የሰብአዊ እርዳታ በሚያቀርቡበት ጊዜ የደህንነት ስጋት ሊያጋጥም እንደሚችል እና የድርጅታቸው ሰራተኞች ይህን እያወቁ ሥራቸውን እንደሚሰሩ ጠቁመው፣ የተቋማቸው ተቀዳሚ ዓላማ የሰብአዊ ድጋፍን በበቂ ሁኔታ በማድረስ የኢትዮጵያ መንግሥትን በማገዝ ሊፈጠር የሚችልን ችግር ማስቀረት መሆኑን ተናግረዋል።
በውይይቱ በሁኔታዎች ላይ የተሻለ ግንዛቤ ማግነታቸውን በውይይቱ የተሳተፉት የተመድ ኃላፊዎች በሰጡት አስተያየታቸው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል ።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!