በአንድ የሰርግ መልስ ዝግጅት ላይ የፈነዳ ቦንብ 15 ሰዎች ላይ ጉዳት አደረሰ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ጅሩ ወረዳ በአንድ የሰርግ መልስ ዝግጅት ላይ የፈነዳ ቦምብ በ15 ሰዎች ላይ ጉዳት ሲያደርስ የአንድ ሰው ህይወት አልፏል።
በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ክፍል ሃላፊ ኮማንደር ተስፋዬ ግዛቸው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት፥ ፍንዳታው የደረሰው ትናንት ከምሽቱ 5 ሰዓት አካባቢ ላም ዋሻ በሚባል ቀበሌ ነው።
ለሰርግ መልስ ተጠርተው የነበሩ ታዳሚዎች በዝግጅቱ ቦታ ላይ እየጨፈሩ እያሉ ከአንድ ግለሰብ ኪስ የወደቀ የጭስ የእጅ ቦምብ በእግር ተነካክቶ ፈንድቷል።
በፍንዳታው የአንድ ሰው ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ፥ ሌሎች 15 ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሶባቸው በደነባ ሆስፒታልና በደብረ ብርሃን ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።
ቦንቡን ይዞ በስፍራው የተገኘው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑም ተገልጿል።
ሕብረተሰቡ ፈንጂና ተቀጣጣይ ነገሮችን ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ይዞ ከመሄድ እንዲቆጠብ ኮማንደር ተስፋዬ አሳስበዋል።
በሰላም አሰፋ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-
https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!