በትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወሰዳል – ባለስልጣኑ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስት ከተቀመጠው የትራንስፖርት ታሪፍ ውጭ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አሽከርካሪዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ በክልሉ ከተሰማሩ 98 የህዝብ ትራንስፖርት ማህበራት ጋር በአዳማ ከተማ ውይይት አካሄዷል።
የክልሉ ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብድልቃድር ሁሴን በወቅቱ እንደገለጹት መንግስት ከወቅቱ የነዳጅ አቅርቦት ጋር ተያይዞ በትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ማስተካከያ አድርጓል።
ይሁን እንጂ ማስተካከያውን ተከትሎ በመንግስት ከተቀመጠው የትራንስፖርት ታሪፍ ውጭ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አሽከርካሪዎች መኖራቸውን ባለስልጣኑ ደርሶበታል ብለዋል ።
ከጭማሪው ጋር ተያይዞ መንግስት ከተመነው ታሪፍ በላይ እየከፈልን ነው በሚል ከህብረተሰቡ የሚነሳ ጥያቄ እየጨመረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ባለስልጣኑ ለህብረተሰቡ ጥያቄ አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት በክልሉ የትራንስፖርት ስምሪት መቆጣጠሪያዎችን በኩታገጠም በማደራጀት የተጠናከረ የቁጥጥር ስራ እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
በመንግስት ከተቀመጠው የትራንስፖርት ታሪፍ ውጭ ያልተገባ ዋጋ በሚጠይቁ አሽከርካሪዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።
ተሽከርካሪዎች ከተፈቀደው የሰው ቁጥር በላይ በመጫን የአደጋ መንስኤ እየሆኑ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ÷ ከተፈቀደው የሰው ቁጥር በላይ በሚጭኑ አሽከርካሪዎች ላይም ጥብቅ ቁጥጥርና እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ባለስልጣኑ የተቀላጠፈ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠትና በዘርፉ የሚስተዋለውን የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት በተለያዩ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች በ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር 11 ዘመናዊ የህዝብ ትራንስፖርት መናሃሪያዎችን እየገነባ እንደሚገኝ አቶ አብድልቃድር ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ የትራንስፖርት ማህበራት በበኩላቸው÷ ዋና አላማቸው ለህብረተሰቡ ተደራሽና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት መሆኑን ገልጸዋል ።
በሚሰጡት የትራንስፖርት አገልግሎት በባለስልጣኑ የተነሱ ችግሮች መኖራቸውን አመልክተዋል።
የመንገዶች ብልሽት፣ የመለዋውጫ ዕቃ ዋጋ መናርና ነዳጅ በጥቁር ገበያ መሸጥ በትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ላልተገባ የዋጋ ጭማሪ መጠየቅ መንስኤዎች ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ጠቅሰዋል ።
በትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ያልተገባ ክፍያ መጠየቅ ተገቢ ባለመሆኑ ድርጊቱ እንዳይፈጸም ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ጠቁመው መንግስት ለችግሩ መንስኤ የሆኑ ክፍተቶችን እንዲፈታ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!