በ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ከ134 ሺህ በላይ የአገር ውስጥ ታዛቢዎች ይሰማራሉ ተብሎ ይጠበቃል -ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛዉን አጠቃላይ ምርጫ ለመታዘብ ለሲቪል ማህበራት እውቅና የመስጠት ስራውን አጠናቀቀ።
በዚህም በ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ከ134 ሺህ 109 የአገር ውስጥ ታዛቢዎች ይሰማራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቦርዱ ገልጿል።
ቦርዱ ምርጫን ለመታዘብ ፍላጎት ላላቸው የሀገር ዉስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፍቃድ ለማግኘት ማመልከቻዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ባወጣዉ ማስታወቂያ መሰረት 111 ድርጅቶች እውቅናን ለማግኘት ማመልከታቸውን አስታውቋል።
ድርጅቶቹ ያቀረቡትን ማመልከቻዎች እና ተያያዥ ሰነዶች በምርጫ ህጉ፣ በወጣዉ ጥሪ እና በመመሪያዉ የተደነገጉትን መስፈርቶች እና ግዴታዎች ያሟሉ ስለመሆኑ እንዲሁም የድርጅቶቹ የማስፈፀም አቅም መገምገሙን ገልጿል።
በዚህም በየደረጃዉ የተጓደሉ ሰነዶችን እንዲያሟሉ በማድረግ በመጀመሪያዉ ዙር ካመለከቱ ከ111 ድርጅቶች መካከል 43ቱ ድርጅቶች ወደ ሁለተኛዉ ዙር እንዲያልፉ መደረጉን ተገልጿል።
ወደ ሁለተኛ ዙር ያለፉት 43 ድርጅቶች በምርጫ መታዘብ ስልት፣የሥልጠና እቅድ እንዲሁም የታዛቢዎች አመራረጥ በተመለከተ በቦርዱ የቅድመ እውቅና ስልጠና(የዓለም አቀፍ ተሞክሮ ታክሎበት) ተሰጥቷቸዉ በመድረኩ ያገኙትን ግብአት በመጠቀም ከላይ የተጠቀሱትን ሦስት የታዛቢነት ስትራቴጂዎችን እንዲያቀርቡ ተደርጎ ከ 43ቱ ድርጅቶች መካከል 36ቱ ስድስተኛዉን አጠቃላይ ምርጫ እንዲታዘቡ ተመርጠዋል፡፡
በዚህም የተመረጡት 36ቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች 13 ሺህ 109 ታዛቢዎችን ማቅረባቸው ተገልጿል።
ከዚህ ዉስጥም በሴቶች ጉዳይ ላይ በሚሰሩ ስምንት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የቀረቡ 61ሺህ 851 ሴት ታዛቢዎች 46 በመቶ ፣ በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ስር የታቀፉ 7 ማህበራትን ያካተተ 244 ታዛቢዎች፣ በሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች የምርጫ ሂደትን ለመታዘብ በተመረጠ 1 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የቀረቡ 100 ታዛቢዎች እና በስሩ 37 ያህል ሲቪል ማህበራትን ያቀፈ የሲቪል ማህበረሰብ ኔትወርክ እንደሚገኙበት አመላክቷል።
በቀጣይ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለተመረጡት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን የሚያዘጋጅ ሲሆን÷ በአጠቃላይ የሚሰማሩትን 134 ሺህ 109 ታዛቢዎችን ለመደገፍ እና ለመከታተልም ስትራቴጂ መንደፉን ከብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!