በአማራ ክልል ከ15 ሚሊየን በላይ የቡናና የፍራፍሬ ችግኞች ለመትከል እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በአማራ ክልል ከ15 ሚሊየን በላይ የቡና፣ የቆላና ደጋ ፍራፍሬ ችግኞች ለመትከል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባለሙያ አቶ አወቀ ዘላለም እንደገለጹት፥ አርሶ አደሩ ከሰብል ልማት በተጨማሪ በሌሎች የኢኮኖሚ አማራጮች ላይ እየተሰማራ ነው።
ዘንድሮ ከ85 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በ14 ሺህ 427 ሄክታር መሬት ላይ የቡናና ፍራፍሬ ችግኞች እንደሚተክሉ ተናግረዋል።
ከሚተከሉት ችግኞች ውስጥ 7 ነጥብ 6 ሚሊየን የቡና ሲሆኑ፥ ቀሪዎቹ የፍራፍሬ ችግኝ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ከ237 ሺህ በላይ የቡና፣ አቦካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ሙዝና ብርቱካን ችግኞች መተከላቸውን አስታውቀዋል።
ተከላው በክልሉ የቡና ልማትን በማስፋፋት ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ እንደሚያሳድግ አቶ አወቀ ተናግረዋል።
እንደባለሙያው ገለጻ፥ የግብርና ባለሙያዎች የአርሶ አደሩን ገቢ ለማሳደግ ሙያዊ ምክር በመስጠት ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ ነው።
በክልሉ ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት ከተተከሉት 10 ነጥብ 7 ሚሊየን ቡናና የፍራፍሬ ችግኞች ከ92 በመቶ በላይ መጽደቃቸው ከግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!