ለ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ሽልማት ተበረከተ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የአቀባበልና የምስጋና መርሃ ግብር ተከናውኗል፡፡
በስነ ስርዓቱ ላይ ለዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የተለያዩ ሽልማቶችና የታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የህልውና ፕሮጀክት መሆኑን የሚያሳዩ የስዕል ስራዎች ተበርክቶላቸዋል።
የዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ቤተሰቦችም በመርሃ ግብሩ የታደሙ ሲሆን ሽልማትም ተበርክቶላቸዋል።
ኢንጂነር ስለሺ በመርሃ ግብሩ ባደረጉት ንግግር በፕሬዚዳንት፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በሌሎች ዲፕሎማቶችና ኢትዮጵያውያን በኩል ቀድመው የተሰሩ ስራዎች ትልቅ ድርሻ መያዛቸውን ተናግረው ይህም ሊደነቅ ይገባል ብለዋል።
እንዲሁም በግድቡ ስራ የተሰማሩ ሁሉም ባለሙያዎች ሊደነቁ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ባለፋት 10 ዓመታት በቴክኒካል፣ በህግ እና በዲፕሎማ ዘርፍ የተሳተፋ ባለሙያዎች ያለ እንቅልፍ ኢትዮጵያ የያዘችው እውነት እንዲያሸንፍ አድርገዋል ነው ያሉት ።
በእውነት የተቀናጀ ስራንና የኢትዮጵያ ህዝብን እውነት ነው ለአለም ያስገነዘብነው ያሉት ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በኒዮርክ ያለው ጉዳይ አሁንም አልተቋጨም ፤ የድርድርና ሌሎች ጠንካራ ስራዎች አሁንም ከፊታችን አሉ ይህንም ተደራዳሪዎችና ባለሙያዎች እንድትረዱ እፈልጋለሁ ሲሉ ገልፀዋል።
በቀጣይ ሂደቶችም ኢትዮጵያን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አቋም በጥንቃቄና በጠንካራ የትብብር መንፈስ ያሰብነውን ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ እንደምንሰራ ለህዝባችን ቃል እገባለሁ ብለዋል።
መርሃ ግብሩን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማት ማዘጋጀታቸው ታውቋል፡፡
በፍሬህይወት ሰፊው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!