የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል ለተሳተፉ የጤናው ዘርፍ ተዋንያን የእውቅና ሳምንት ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 8 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከልና መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን በመስጠት አስተዋፅኦ ላበረከቱ የጤና ባለሙያዎችና የክብካቤ ሰራተኞች የምስጋናና እውቅና ሳምንት እንደሚካሄድ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የእውቅና ሳምንቱ ከሐምሌ 11 እስከ 17 ቀን 2013 ዓ.ም “የጤናው ዘርፍ ሰራተኞች ሳምንት” በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የእውቅና ሳምንቱን አስመልክተው እንዳሉት÷ የጤና ባለሙያዎችና የክብካቤ ሰራተኞች ህይወታቸውን በመክፈል ጭምር ወረርሽኙን ለመከላከል ሌት ተቀን ደክመዋል፤ አሁንም እየደከሙ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በቫይረሱ የተያዙ ዜጎችን ለማዳን ህብረተሰቡን ያስተማሩና ሌሎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶች እንዳይቋረጡ ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጤናው ዘርፍ ተዋንያኖችም ምስጋና እንደሚገባቸው የተናገሩት ዶክተር ሊያ የእውቅና ሳምንቱም ይህን ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የእውቅና ሳምንቱ አዲስ አበባ ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚከበር ሲሆን÷ “የጤናና የጤና ክብካቤ ሰራተኞች ደህንነት ይጠበቅ” የሚሉና ሌሎች ተያያዥ መልዕክቶች ይተላለፋሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!