Fana: At a Speed of Life!

ሕጻናትን ወደ ጦርነት የመማገድ የህወሃትን የወንጀል ድርጊት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወግዘው ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን እየፈጸመ ያለውን ሕጻናትን በአደንዛዥ ዕጽ በማስከር ወደ ውጊያ የመማገድ ወንጀል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያወግዘው እንደሚገባ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አመለከተ።
ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በመጣስ ህጻናትን ወደጦርነት ያሰለፈውን የሕወሃት ሃይል በዓለም አቀፍ ወንጀል እንዲጠየቅም ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ተባባሪ መሆን እንዳለባቸው ገልጿል።
ከሰሞኑ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን በተጻረረ መልኩ መልከ ብዙ ወንጀሎችን እየፈጸመ ስለመሆኑ በገሃድ ተስተውሏል።
የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ የሕወሃት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ ከፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ባለፈ አሁን ደግሞ ህጻናትን በአደንዛዥ ዕጽ አስክሮ ለጦርነት እያሰለፈ የወንጀል ድርጊት እየፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።
“እድሜያቸው ለውጊያ ያልደረሱ የነገ ሃገር ተረካቢ ህጻናትን ወደጦርነት ማስገባት ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተጻረረ በመሆኑ ሊወገዝ የሚገባው ድርጊት ነው” ብለዋል።
ህጻናት የነገ ሃገር ተረካቢዎች እንጂ ካለ እድሜያቸው በጦርነት እንዲሞቱ ማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደነገገ ወንጀል ቢሆንም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግን ሽብርተኛው የህወሃት ቡድን እየፈጸመ ያለውን ዓለም ቀፍ ወንጀል በዝምታ መመልከቱን አንስተዋል።
ይህ ህጻናትን ወደ ውጊያ የማስገባት ወንጀልን በዝምታ ማለፍ በሃገር ሞራል ላይ መረማመድ እንደሆነም ገልጸዋል።
ይህንን ሰብዓዊ ወንጀል ያለማውገዝና የድርጊቱ ተባባሪ የመሆን ዝንባሌ የውጭ ሃይሎች ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት እንዳትለማና ህዝብ ከህዝብ እየተጋጨ እንዲኖር ፍላጎት እንዳላቸው እንደሚጠቁምም አንስተዋል።
“የሽብር ቡድኑ እድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱ ታዳጊዎቸን ወደውጊያ በማስገባት ዓለም አቀፍ ወንጀል እንዲጠየቅ ልንሰራ ይገባል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.