Fana: At a Speed of Life!

የብስክሌት ትራንስፖርትን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የብስክሌት ትራንስፖርትን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በዩ ኤን ሃቢታት አስተባባሪነት በኢትዮጵያ የሚሰሩ የመንገድ ዲዛይኖችን ማሳደግ በሚል መሪ ቃል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱም የብስክሌት ትራንስፖርት ለማስፋፋት ለሁለት ዓመታት የተሰሩ ስራዎችና የቀጣይ አቅጣጫዎች ቀርበው በተሳታፊዎች አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በቀጣይ በመዲናዋ 730 የብስክሌት መስመር ዝርጋታ፣ 103 የብስክሌት ስቴሽን ግንባታ እና በየ10 ነጥብ 3 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ብስክሌት መጋራት የሚያስችል ስርዓት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በመላ ሀገሪቱም የከተሞችን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የብስክሌት ትራንስፖርት ተደራሽ እንደሚደረግ በውይይቱ ተመላክቷል፡፡
የትራንስፖርት ር ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ÷ በመላ ሀገሪቱ ሞተር አልባ ትራንስፖርትን ተደራሽ ለማድረግ የ10 ዓመት ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
ስትራቴጂውን መነሻ በማድረግም ማህበረሰቡ ብስክሌት እንዲጠቀምና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርግ በየወሩ መጨረሻ እሁድ የብስክሌተኞችና እግረኞች መርሃ ግብር እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሞተር አልባ ትራንስፖርት የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ወይዘሮ ዳግማዊት ማሳሰባቸው ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የዩ ኤን ሃቢታት ዋና ዳይሬክተር ማሃድ ሻሪፍ በበኩላቸው ÷ በመዲናዋ የተጀመሩትን የብስክሌት መሰረተ ልማቶች እንደመነሻ በመውሰድ በመላ ሀገሪቱ የማስፋፋት ስራ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.