ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መተባበር እና መተማመን እንዲኖረው ይሰራል-የሰላም ጓድ ልዑክ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በዳያስፖራው መካከል ያለውን መከፋፈል ለማስወገድ እና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መተባበር እና መተማመን እንዲፈጠር ለማድረግ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ የዳያስፖራ የሰላም ጓድ ልዑክ ገለጸ፡፡
የሰላም ጓድ ልዑክ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ብሩክ ሃይሉ በሻህ ÷ ልዑኩ ባለፉት ሶስት ሳምንታት በኢትዮጵያ ባደረገው ቆይታ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ልዑኩ ከዘጠኝ ወራት በፊት የተቋቋመ እና በዳያስፖራው እና በሃገሩ መካከል ድልድይ የመሆን ዓላማ ያለው ነው ብለዋል።
በሃገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት ውስጥ የበኩሉን የመወጣት ፍላጎቱን በውጭ ሆኖ ከመመልከት ይልቅ በአካል በመገኘት ሁኔታዎችን ለማጤን ጭምር ወደ ሃገር ቤት መምጣቱን አንስተዋል።
13 ሲቪክ ማህበራት ተጣምረው የፈጠሩት ልዑኩ በሰላም እጦት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በተለያዩ ጣቢያዎች ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በአጣዬ መጠለያ ጣቢያ፣ በከሚሴ አርጡማ ፋርሲ ወረዳ ዲምቱ ጨርቆሳ መጠለያ ፣ በኮንሶ ገለቦ መጠለያ ጣቢያ እና በደራሼ ልዩ ወረዳ ጋቶ መጠለያ ጣቢያ በመገኘት የብርድ ልብስና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ አድርጓል።
ከውጭ ሃገራት እና ከሃገር ቤት ሆነው ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
የሰላም ጓድ ልዑኩ በሶማሌ ክልል በመገኘትም ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ጋር ቆይታ በማድረግ በክልሉ ስላለው ሰላም እና ይህንን ተሞክሮ ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል።
ልዑኩ በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው የህግ ማስከበር እርምጃም የሃገሪቱን ሉዓላዊነት የሚያስጠብቅ መሆኑን እንደሚያምን ነው የገለጹት።
ልዑኩ በቆይታው ከተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የተቋማት መሪዎች እና የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል፡፡
በምስክር ስናፍቅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!