ሰርገው የሚገቡ ሽፍቶችን ለመደምሰስ ቅንጅታዊ ስልት ላይ ውይይት ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ለማደናቀፍ ሰርገው የሚገቡ የህወሓት ተላላኪ ሽፍቶችን ለመደምሰስ በሚካሄዱ ዘመቻዎች ላይ የጋራ ወይይት መካሄዱ ተገለፀ፡፡
ውይይቱን ያካሄዱት የመተከል ዞን እና አጎራባች የአማራ ክልል ወረዳዎች ሲሆኑ÷ ተቀናጅተው በጋራ መስራት በሚያስችላቸው ሁኔታ ላይ ነው የመከሩት፡፡
ከአማራ ክልል የአዊ ዞን፣ የጃዊ፣ የጓንጓ ወረዳ እና ከመተከል ዞን ከመከላከያ ተመላሽ የሰራዊት አባላት ፣ ታጣቂዎች እና ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ተቀናጅተው የህዳሴውን ግድብ እና መዳረሻ ቀጠናዎችን ከሽፍቶች ማፅዳት በሚያስችላቸው ጉዳይ ላይ ነው ውይይቱ የተካሄደው።
የዞኑ የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት ዋና ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ተልዕኮው ኢትዮጵያን የማዳን ዘመቻ አካል መሆኑንና ሁሉም ዜጋ በጋራ መረባረብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በግዳጅ ቀጣናው የሚገኝ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥም በበኩላቸው ÷ የሁለቱ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ግዳጃቸውን ተቀናጅተው በጋራ የሚፈፅሙበትን ሀሳብ በማቅረብ ውይይት ተደርጎበታል።
የፀጥታ ኃይሎቹ በዞኑ በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት በበላይነት የሚታዘዙ መሆናቸውን የክፍለ ጦር አዛዡ መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የተገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!