በሀረሪ በ77 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው ዘመናዊ የቄራ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት በከተማ ተቋማዊና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በሀረሪ ክልል ሶፊ ወረዳ በ77 ሚሊየን ብር የተገነባው ዘመናዊ የቄራ አገልግሎት መስጫ ህንፃ ተመርቋል፡፡
በመርሃ ግብሩ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ተገኝተዋል፡፡
ኢንጂነር አይሻ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በከተሞች ማስፋፊያና ፕሮግራም የከተሞችን አቅም ከማሳደግ አኳያ በ117 ከተሞች እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በጥንታዊቷ ሀረር ከተማ ከቄራ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ይስተዋል የነበረውን ችግር ለመፍታት ዘመናዊ የቄራ አገልግሎት መስጫው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው÷ የክልሉን ህዝብ መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታትና ድሃ ተኮር የሆኑ የመሰረተ ልማት ማስፋፋት ላይ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ውስብስብ ችግሮች ሳቢያ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ረዥም ጊዜ የወሰደ ቢሆንም በቀጣይ የቄራውን ውስጣዊ አደረጃጀት በማስተካከል ስራውን በተሟላ መልኩ እንዲያከናውን እንደሚደረግ ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡
ይህ ዘመናዊ የቄራ አገልግሎት መስጫ ህንፃ ጥራቱና ጤናው የተጠበቀ ስጋ ለህብረተሰቡ እንዲደርስ ያስችላል ያሉት ደግሞ የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራአስኪያጅ አቶ በቀለ ተመስገን ናቸው፡፡
በተጨማሪም ቄራው በሰዓት 40፣ በቀን ደግሞ 980 በሬዎችን አርዶ እንደሚያወጣ ገልፀዋል፡፡
ቄራው ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጥርና ተረፈ ምርቶቹም ተመልሰው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የሚያስችል አሰራር እንደተዘረጋ በምረቃ ስነስርዓቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
በምርቃ ስነስርዓቱ ላይ የተሳተፉ እንግዶች በቄራው ቅጥር ግቢ ውስጥ ችግኞችን በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
በተሾመ ኃይሉ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!