Fana: At a Speed of Life!

የአሸባሪዎቹ ጥምር ጥቃት ከወለጋ እስከ ወሎ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የአሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ ጥምር ጥቃት ሰለባዎች ከወለጋ እስከ መርሳ-ደሴ ረጅሙ የሰቆቃ ጉዞን እያሳለፉ ነው፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ተወልደው ያደጉት ወይዘሮ ጸሀይነሽ ካሳው ሶስት ጉልቻ መስርተው መኖር ከጀመሩ ድፍን ሰላሳ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡

በትዳር ዘመናቸው የሁለት ዓመቷን ህጻን ኢክራምን ጨምሮ ሶስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡

ዘመናትን ባስቆጠረ ኢትዮጵያዊነት ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ወልደው ተዋልደው በጋብቻ ተጋምደው የኖሩ እናት ናቸው፡፡

ዛሬ አሸባሪው ህወሃት በፈጠረው መንገድ በማንነታቸው ዛሬ መከራ በዝቶባቸዋል፡፡

ከእለታት አንድ ቀን አንድ አዲስ እንግዳ ክስተት ተፈጠረ፤ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በጉሊሶ ወረዳ የዲላጎ ጎላቃዋ ቃራ ቀበሌ የአማራ ማንነት ያላቸው አርሶ አደሮች መላዕከ ሞትን በያዙ እኩይ ታጣቂዎች አስቸኳይና አስገዳጅ ስብሰባ ተጠሩ፡፡

የስብሰባው አጀንዳ ያልተረዱ ምስኪን አርሶ አደሮችም ወንድ ሴት ሳይለዩ ግማሾቹ በጥርጣሬ ገሚሶቹ በመደናገር ለስብሰባ ወደተጠሩበት አዳራሽ ገቡ፡፡

በቅጽበት ነገሮች ሁሉ ተለዋወጡ፤ አብሮ ዘመናትን ካሳለፈው የኦሮሞ ህዝብ በወጡና እኩይ አላማ ባነገቡ የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎች ከ200 በላይ ንጹሃን አርሶ አደሮች በማንነታቸው በግፍ ተጨፈጨፉ፡፡

ወይዘሮ ጸሀይነሽ ካሳው የሆነውን እንዲህ ያስታውሳሉ “ጥቅምት 22 ቀን ምሽት ለስብሰባ ተጠራን ከስብሰባው እንደገባን በታጠቁ ሰዎች በሩ ተዘጋብን ዛሬ እንገላችኋላን እናንተ እስከዛሬ ኖራችሁ ከዚህ በኋላ ሀብት ንብረት ሳትሉ ወደ ሀገራችሁ ብለውን በመቅጽበት የጥይት ላንቃ ከፈቱብን”፡፡

የስድስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ አረጋሽ አሊና ወይዘሮ ደመቅ ሁሴንም እንደ ወይዘሮ ጸሀይነሽ ሁሉ ነዋሪነታቸው ወለጋ ቢሆንም “ለ200 ሰው ሁለት መቶ ጥይት አናወጣም” ከሚሉ ጨካኞችና እብሪተኞች ግድያ ተርፈው መርሳ መድረሳቸውን ይገልፃሉ፡፡

በዚያች ክፉ ቀን ተፈናቅለው አማራ ክልል መርሳ የመጠለያ ኑሮን እየገፉ እንደነበር ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከወለጋ በአሸባሪው ሸኔ ሃብታቸው ተዘርፈው የቀረው ተቃጥሎባቸው ህይወታቸው በተዓምር ያተረፉት እነዚህ ንጹሃን ዜጎች ዛሬም የመከራ ቀንበሩ ከትከሻቸው ላይ አልወረደላቸውም፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.