የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት 400 ሺህ ቶን ስንዴ ከውጭ ተገዝቶ እየተጓጓዘ ነው
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት 400 ሺህ ቶን ስንዴ ከውጭ ተገዝቶ ወደ አገር ውስጥ እየተጓጓዘ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የማክሮ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ማሞ እስመላለም ተናገሩ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በየወሩ በሚዘጋጀው ‘አዲስ ወግ’ የአንድ ርእሰ ጉዳይ የውይይት መድረክ “ፅናት ለሀገር ህልውና” በሚል መሪ ሃሳብ ውይይት አካሄዷል።
በውይይቱ ላይ የመነሻ ጽሁፉ ያቀረቡት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የማክሮ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አማካሪ ማሞ እስመላለም፤ አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ባለፉት ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ላይ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።
ነገር ግን “የዋጋ ንረት አሁንም ቢሆን ያልተሻገርነው ፈተና ነው” ያሉ ሲሆን÷ ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ በአገር ውስጥ ያለው የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣምና በውጭ አገራት ያለው የሸቀጦች ዋጋ መጨመርን በምክንያትነት አንስተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የብረት ዋጋ 32 በመቶ፣ የነዳጅ ደግሞ 41 በመቶ እንዲሁም የምግብ ሸቀጦች 13 በመቶ ጭማሪ ማስመዝገባቸውንም የጠቀሱት አቶ ማሞ መንግስት የዋጋ ንረቱ በዜጎች ኑሮ ላይ ጫና ሳይፈጥር በጊዜያዊነት ለመፍታት 400 ሺህ ቶን ስንዴ ግዥ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
ከዚህም ወስጥ 40 ሺህ ቶን የሚሆነው ወደብ ላይ መድረሱንና ወደብ ከደረሰው 18 ሺ ቶኑ ደግሞ በአገር ውስጥ መጋዘኖች መከማቸቱን ተናግረው÷ በተጨማሪ 36 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ግዥ ተከናውኗል ነው ያሉት።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በተለይ በፋይናንስ ዝውውሩና በፋይናስ ስርዓቱ ላይ የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!