Fana: At a Speed of Life!

አድዋን የደገመች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ለማስረከብ ከምን ጊዜውም በላይ አካባቢያችንን መጠበቅ አለብን-ወ/ሮ ዘርፈሸዋል ንጉሴ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)አድዋን የደገመች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ለማስረከብ ከምን ጊዜውም በላይ አከባቢያችንን በመጠበቅ ረገድ የድርሻችንን መወጣት አለብን  ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አፈ ጉባኤ  ወይዘሮ ዘርፈሸዋል ንጉሴ ተናገሩ።

“አንድ ሆነን ድምፃችንን እናሰማለን፤ አንድ ሆነን ጠንካራ ክንዳችንን እንሰነዝራለን!” በሚል መሪ ቃል ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ሴቶች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ  ውይይት አድርገዋል።

አፈ ጉባኤዋ በውይይቱ ባስተላለፉት መልዕክት፥  ጁንታው ኢትዮጵያን ያለ ልክ በመካድ እና ሀገር የመከፋፈል ዓላማ አንግቦ እያደረገ ባለው ጦርነት እኛ ሴቶች የትኛውንም መስዋዕትነት ቢያስከፍልም ወደኋላ የማንል መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል ።

ወይዘሮ ዘርፈሸዋል  አያይዘውም ጁንታውን እየተከተለ ድል እየነሳ ያለውን የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ልዩ ልዩ የጸጥታ አካላትን የመደገፍ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አሳስበዋል ።

ጁንታውና የትግራይ ተወላጅ አንድ እንዳልሆኑ የገለጹት የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ም/ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ፥ አሁን ያለው ጦርነት የኢትዮጵያን አንድነትና ልማት በማይፈልጉ የውጭ ሀይሎች በእጅ አዙር የሚደረግ ጦርነት መሆኑን በመገንዘብ ሁላችንም በመተባበር፣ በመተጋገዝ እና በእህትማማችነት መንፈስ በያለንበት የድርሻችንን ሚና መወጣት ከቻልን በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ወቅት ማለፍ እንችላለን በማለት ገልጸዋል ።

እኛ እያለን ልጆቻችን ሀገር አያጡም ያሉት የመድረኩ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያን ለመበታተን ቆርጦ የተነሳውን አሸባሪ የህወሓት ቡድንን ስንቅ ከማዘጋጀት ጀምሮ እስከ ግንባር ድረስ በመሰለፍ ኢትዮጵያ ለማዳን ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ ነን ሲሉ ገልጸዋል።

ጁንታው መበስበስ እንጂ ማበብ አይፈልግም ያሉት የከተማዋ ሴቶች አካባቢያቸውን በንቃት በመጠበቅ እና ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን መቆማቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል ።

በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረቱን ያደረገው የከተማዋ ሴቶች የውይይት መድረክ ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ዘርፈሸዋል ንጉሴ በተጨማሪ የሴት አደረጃጀት ኃላፊዎችና የከተማዋ ሴቶች  የተገኙ ሲሆን የጋራ የአቋም መግለጫ በማውጣት መጠናቀቁን ከከተማዋ ፕሬስ ሰክሬተሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.