Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ካዘመመችበት ቀና የምትልበት ጊዜ አሁን ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስራች ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሰየሙት ዶክተር ዐቢይ አህመድ፥ ኢትዮጵያ ካዘመመችበት ቀና የምትልበት ጊዜ አሁን ነው ሲሉ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመስቀል አደባባይ በርካታ የአፍሪካ መሪዎችና አያሌ የአዲስ አበባ ከተማና አካባቢዋ  ነዋሪዎች በተገኙበት የበዓለ ሲመታቸው ሥነ ሥርዓት  ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ግልጽና ተዓማኒ ምርጫ ተካሂዶ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያገኘ መንግሥት ምስረታ ላይ ስለደረስን እንኳን ደስ አለን ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ጠላቶቿን ድል አድርጋና ችግሮቿን ተሻግራ አንገቷን ቀና አድርጋ የምትጓዝበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና በምታደርገው ጉዞ የወዳጆቿን አጋርነት ትሻለች ፤ ነገር ግን ሉዓላዊነቷን እና ነፃነቷን በሚነካ ማንኛውም ጉዳይ ላይ ድርድር አይኖራትም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው፥  ኢትዮጵያ ከፊት ለፊቷ ያለውን ቆሻሻ  አስወግዳ፥  አቧራውን ጠርጋ ወደ ብልጽግና ትጓዛለች ሲሉም አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፥ በምርጫው የተመዘገበው ድል የአንድ ፓርቲና የመንግስት ብቻ ሳይሆን፥ እንደ ህዝብ በአንድነት ያሸነፍንበት መሆኑን ተገንዝበን ወደ ከፍታው ምዕራፍ በአንድነት መጓዝ አለብን ሲሉም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት የአሸናፊዎች ብቻ እንዳይሆን መንግሥታቸው ሁሉን አአካታችና አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲሰፍን በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫው ሂደት ለመፍጠር የተሞከሩትን እንቅፋቶች አኩሪ በሆነ መንገድ ተወጥቶታል ነው ያሉት፡፡

ለአፍሪካውያን ባስተላለፉት መልዕክትም ፣ “ውድ አፍሪካውያን እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ከሚያጋጩን ነገር ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ነገር ብዙ ናቸው ፤ አንድ ከሆን ጠላቶቻችን ከንስር ፊት እንደቆመች ድንቢጥ ናቸው” ብለዋል፡፡

ጨምረውም ጥቅሟን የምታሰጠብቅ አህጉር እንድትኖረን በህብርት ጥረት ማድርግ አለብንሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

ቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ከፍ የምትልበት ጊዜ እንደሚሆን በንግግራቸው አንስተው÷ ኢትዮጵያ ገናናው ስሟ በዓለም በስፋት እንዲናኝ የምታደርግበት ይሆናል ብለዋል፡፡

አሁን የተጋረጡብንን ችግሮች የምንወጣውም በጋራ በመስራት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ÷ የውስጥ ሽኩቻችን ለጠላቶቻችን ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጥር መጠንቀቅ አለብን ሲሉም መክረዋለ፡፡

ለአፍታ እንኳ ሳንዘናጋና ሳናንቀላፋ ለአገራችን ህልውና ደህንነትና ብልጽግና በቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉም ቃል ገብተዋል።

ለዘመናት የተከማቹ የመጡትን የኢኮኖሚ ችግሮች ለማሸነፍ በአንድነት መነሳት ይኖርብል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ መንግሥታቸው የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራቸው ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው የዋጋ መናርን መቆጣጠር እንደሆነም አስምረውበታል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ መንግስታቸው በትጋት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

ከሃዲዎች በፈፀሙት የእብሪት እርምጃ  ምክንያት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተከሰተው ግጭት አገራችን እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ከፍላለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ያጋጠሙን የውስጥ ጠላቶች ኢትዮጵያ -ጠል የሆኑ  አረመኔዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዚህም ወደን ሳይሆን ተገደን የሀገራችንን ህልውና ለማረጋገጥ የገባንበት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ሲሉም አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአገራቸው ህልውና እና ሰላም በአንድነት ለቆሙትና የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ለሆኑት የመከላከያና የፀጥታ አካላት ውለታቸው ምን ጊዜም የማይረሳ እንደሆነም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያን በማድነቅ ስሟን ደጋግመው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለኝን ታላቅ

አክብሮትና ምስጋና እገልጻለሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.