“ህገ ወጥ የደላላ ሰንሰለትን በመቁረጥ የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ እንሰራለን “-ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)”በአምራቾችና ሸማቾች መካከል ያለውን ህገ ወጥ የደላላ ሰንሰለት በመቁረጥ የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ እንሰራለን ” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመራው ልዑክ ባለፉት ቀናት በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን እና በምስራቅ ሸዋ ዞን በኩታ ገጠም የለሙ ማሳ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
በጉብኝት መርሀግብር ላይ የተሳተፉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት÷ በገበያ ውስጥ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ የሚያደርጉ ህገ ወጥ ደላሎች ይገኛሉ ፡፡
እነዚህን ህገወጥ ደላሎች ሰንሰለት አምራቹንና ሸማቹን ማህበረሰብ እየጎዱ ይገኛሉ ያሉት ከንቲባዋ ህገ ወጥ የደላላ ሰንሰለቱን በመቁረጥ የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ የንግድ ስርዓቱን በማስተካከል አምራቾች እና ሸማቾች ቀጥታ የሚገናኙ የንግድ ማዕከላትን በአምስቱም መግቢያ በሮች እና በተለያዩ ቦታዎች የመገንባቱን ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባዋ መግለፃቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በዘንድሮው በጀት ዓመትም ከሶስት በላይ ግዙፍ የገበያ ማዕከላትን ለመገንባት እቅድ መያዙን እና ከክልል አምራች ገበሬዎች ጋር ቀጥታ ግንኙነት በመፍጠር ሸማቹ በሳምንቱ መጨረሻዎች ወደ ማዕከላቱ በመሄድ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን እንዲገበያይ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!