የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዶንባስ ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሩን ይፋ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን በመገንጠል ራሷን ነፃ አገር አድርጋ ባወጀችው ዶንባስ ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ማስጀመራቸዉን ይፋ አደረጉ።
ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው ልዩ ወታደራዊ ዘመቻው የዶንባስ ህዝብ ከሞስኮ ወታደራዊ ድጋፍ መጠየቁን መሰረት በማድረግ መጀመሩን ነው ያስታወቁት።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር መሰረት እና የዶኔትስክ እና የሉጋንስክ ሪፐብሊኮች ከሩሲያ ጋር በገቡት የወዳጅነት ስምምነት መሰረት እየተፈፀመ መሆኑንም አመልክተዋል።
አያይዘውም ዩክሬንን ፀረ ሩሲያ ከሆኑ ናዚዎች ማፅዳትንም ወታደራዊ ዘመቻ ዓላማ ማድረጉን አስታውቀዋል።
ይህንንም መግለጫ ተከትሎ በተለያዩ የዩክሬን ከተሞች ፍንዳታዎች ተሰምተዋል።
ወታደራዊ ዘመቻው የተጀመረው ሩሲያ ለሁለቱ ሪፐብሊኮች እውቅና መስጠቷን ተከትሎ ነው።
ዩክሬን የኔቶ አባል ለመሆን እንቅስቃሴ መጀመሯን ተከትሎ በሞስኮ እና ኬይቭ መካከል ውጥረት ተፈጥሯል።
በተለይም ሩሲያ ለሁለት ተገንጣይ የዩክሬን ግዛቶች እውቅና መስጠቷ ችግሩን ይበልጥ አወሳስቦታል ነው የሚባለው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም አውሮፓውያ እና ሌሎች የውጭ ሃይሎች በሩሲያ -ዩክሬን ግጭት ላይ ጣልቃ የሚገቡ ከሆኑ ውጤት የከፋ ይኖናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል ፕሬዚዳንት ፑቲን፡፡
የልዩ ወታደራዊ ዘመቻው መታወጅን ተከትሎ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የዓለም ህዝብ ዩክሬንን በፀሎት እያሰበ ነው ማለታቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል።