Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል የተገነባውን የኩላሊት እጥበት ማዕከል መረቁ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 22 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል የተገነባውን የኩላሊት እጥበት ማዕከል መረቁ።

በምረቃው መርሐ ግብር ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተገኝተዋል።

አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየሰራ የሚገኘው የከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊና ብቁ የጤና ተቋማት በመገንባት ተመጣጣኝና ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ተብሏል።

የኩላሊት እጥበት ማዕከሉ ቀድሞ በሁሉም የመንግስት ሆስፒታሎች ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በአምስት እጥፍ እንደሚያሳድገው መገለጹን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ወቅት ፥ ሰው በሚያውቀው በተማረበት በርካታ ድንቅ ስራ ሊሰራ እንደሚችል ዛሬ አይቻለሁ፤ ባየሁትም ነገር ተደስቻለሁ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ፕሮፌሽናሊዝም ጠፍቶ በመቆየቱ ምክንያት ማየት የሚገባንን ነገር ለብዙ ጊዜ ማየት ሳንችል ቆይተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥በምንችለው በተማርነው ሁላችንም አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለከተማ አስተዳደሩም እንደ አዲስ ሲዋቀር ከተሰጠው ተልእኮ ውስጥ አንዱ የጤና ስራ ማስፋፋት መሆኑን ገልፀው ፥ አሁን ተስፋ ሰጪ ነገሮችን ማየት መቻላቸውን አንስተዋል።

ሆስፒታሎች ንፁህና ለሁሉም ሰው የሚስማማ መሆን አለባቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ መኖሪያዎች ከተማዋ በአጠቃላይ ንፁህና ያማሩ እንዲሁም አረንጓዴ መሆን አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ፥ የኩላሊት ህመም የጤና ስርዓቱን እየፈተነ ያለ ህመም በመሆኑ ምክንያት የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት ምንም ገቢ የሌላቸውንና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች በሁሉም የመንግስት ሆስፒታሎች ነፃ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አውስተው፥ በዚህም በሁለቱ ዓመታት 24 ሚሊየን ብር ያህል ድጎማ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

ከንቲባዋ አክለውም ፥ አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ በአጋርነት መስራት አስፈላጊነት ታምኖበት ህግ ማዕቀፍ ወጥቶለት እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለተጨማሪ መረጃ ሊንኩን ይጫኑ፡-

https://www.youtube.com/watch?v=f-GRozi5rdw

ይህ የኩላሊት መድከም ላለባቸው ዜጎች ትልቅ የምስራች ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ፥ ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎቶችን እናሰፋለን ብለዋል፡፡

ስራው እውን እንዲሆን የላቀ አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.