የግል ት/ቤቶች ያደረጉት የክፍያ ጭማሪ ከወላጆች ጋር መግባባት ላይ ሳይደርሱ ወደ ተግባር መግባት አይችሉም- ባለስልጣኑ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግል ትምህርት ቤቶች ያደረጉት የክፍያ ጭማሪ ከወላጆች ጋር በቂ መግባባት ሳይደርሱ ወደ ተግባር መግባት እንደማይችሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ባለስልጣኑ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የ2016 ዓ.ም የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ጭማሪን አስመልክቶ ከሁሉም ትምህርት ቤት ባለቤቶች ጋር ውይይት መደረጉን አንስቷል፡፡
በዚህም የክፍያ ጭማሪው በትምህርት ቤቱ እና በወላጆች ውይይት እና መግባባት መሰረት ያደረገ እንዲሆን በጋራ ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ በመዲናዋ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የክፍያ ጭማሪውን በተመለከተ ከወላጆች ጋር በቂ ስምምነት ያልደረሱ መሆኑን በውይይቱ ወቅት በተደረገ ምልከታ መረጋገጡን ጠቁሟል፡፡
ስለሆነም ትምህርት ቤቶች የ2016 ዓ.ም የክፍያ ጭማሪን ከወላጆች ጋር በቂ መግባባት ላይ ሳይደርሱ ወደ ተግባር መግባት የማይችሉ መሆኑን ነው ያስገነዘበው፡፡
በአንጻሩ ትምህር ቤቶች ከተማሪ ወላጅ ተወካዮች እና ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር ውይይት በማድረግ በሚቀመጠው የጋራ አቅጣጫ መሰረት ብቻ ወደ ተግባር መግባት እንደሚችሉም አስታውቋል፡፡