ኢትዮጵያ በ3ኛው የቻይና-አፍሪካ የንግድ እና ኢኮኖሚ ኤክስፖ ላይ እየተሳተፈች ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በ3ኛው ቻይና-አፍሪካ የንግድ እና ኢኮኖሚ ኤክስፖ ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡
በቻይና ሁናን እየተካሄደ በሚገኘው ኤክስፖ ላይ የ53 አፍሪካ ሀገራት ተወካዮች እና የበርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በመድረኩ ባደረጉት ንግግር÷ኢትዮጵያ በምግብ ምርት እና በንግድ ልውውጥ ሒደት የሚጠበቅባትን መስፈርት ለማሟላት ጥረት እያደረገች ነው ብለዋል፡፡
የቻይና እና የአፍሪካ ሀገራት ትብብር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የተናገሩት ሚኒስትሩ÷በቀጣይ የጋራ ተጠቃሚነትን ባስጠበቀ መልኩ ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው በቻይና ቻንግሻ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ቻይና ዩንግጆ የደረቅ ወደብ ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ኮንፍረንስ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩም አምባሳደሩ÷ በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ አስመልክተው ገለጻ ማድረጋቸውን ከቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡