በክልሉ በ984 ሺህ ሄክታር ለውጭ ገበያ የሚውል ቦሎቄና ሰሊጥ እየለማ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ከ984 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ለውጭ ገበያ የሚሆን ቦሎቄና ሰሊጥ ልማት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።
በቢሮው የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ሙስጠፋ ሁሴን እንደገለጹት÷በክልሉ ከምግብ እህል በተጓዳኝ ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶች ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በተለይም ቦሎቄ፣ ሰሊጥና ሱፍን ጨምሮ ጥራጥሬና የቅባት እህሎች ትኩረት ከተሰጣቸው የሰብል ዓይነቶች ናቸው ብለዋል።
በተያዘው የመኽር እርሻም በክልሉ 984 ሺህ 907 ሄክታር በቦሎቄ፣ በሰሊጥና ሱፍ ሰብል መሸፈኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በዚህም ቦሎቄ 657 ሺህ 664 ሄክታር፣ ሰሊጥ 294 ሺህ 244 ሄክታር እንዲሁም ሱፍ 32 ሺህ 999 ሄክታር መሬት መሸፈኑን ተናግረዋል።
ከምግብ እህል ልማት በተጓዳኝ ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችንም ለማሳደግ በክልሉ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላይ የተለያዩ መርሐ ግብሮች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡
ከዘርፉም ከ6 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ዳይሬክተሩ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡