ኢትዮጵያ የሽብር ቡድኑ አልሸባብ በሶማሊያ ባደረሰው ጉዳት የተሰማትን ሐዘን ገለጸች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ አሸባሪው አልሸባብ በሶማሊያ ላይ ባደረሰው ጉዳት የተሰማትን ጥልቅ ሐዘን ለሀገሪቱ መንግሥት እና ሕዝብ ገለጸች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ባስተላለፉት መልዕክት÷ አሸባሪው አልሸባብ ከሰሞኑ በሶማሊያ በፈፀመው የሽብር ጥቃት በደረሰው ጉዳት ኢትዮጵያ ማዘኗን አስታውቀዋል፡፡
በሽብር ቡድኑ ጥቃት ምክንያት በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋት እና አካል ጉዳት የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልፀዋል።
በልምምድ ወቅት ወታደራዊ መኮንኖችን ኢላማ በማድረግ የተፈፀመውን ጥቃት የወንጀል ተግባር ነው ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ይህን የወንጀል ተግባር ኢትዮጵያ በፅኑ ታወግዛለች ብለዋል።
በተመሳሳይ አሸባሪው አልሸባብ ከሰሞኑ በሶማሊያ በፈፀመው የሽብር ጥቃት በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች እና በባህሬን ወታደራዊ መኮንኖች ላይ በደረሰው የሕይወት መጥፋት እና የአካል ጉዳት ኢትዮጵያ ሐዘኗን ገልጻለች፡፡
አምባሳደር ታዬ ለሁለቱ መንግሥታት ባስተላለፉት የሐዘን መልዕክት የሽብር ተግባሩን ኢትዮጵያ በፅኑ እንደምታወግዝ አስታውቀዋል።
ጥቃቱ አልሸባብ በሶማሊያ እና በክፍለ አኅጉሩ ደኅንነት አደጋ መደቀኑን በግልፅ ያረጋገጠ መሆኑን ጠቅሰው፥ የአካባቢው ሀገራት በፀረ-ሽብር ላይ የሚያደርጉትን ትብብር ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አመላካች ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
የሶማሊያን ሰላም እና ደኅንነት በጋራ ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ትብብሯን አጠናክራ በቁርጠኝነት እንደምትቀጥልም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!