በአዲስ አበባ የፍርድ ቤት ዳኛ የነበረው ተስፋዬ ደረጄ ከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተበት
አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዳኛ እና የኢንስፔክሽ ኃላፊ የነበረው ተስፋዬ ደረጄ ላይ ከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቷል።
ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙሰና ጉዳዮች ጀነራል ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ የሙስና ወንጀሎችን ለመቆጣጠር እና ለመከላክል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 1 እና 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፏል በማለት በከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል ዝርዝር ክስ አቅርቦበታል።
በዚህም ተከሳሹ በአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች የፍርድ ምርመራና ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና ዳኛ ሆኖ ሲሰራ የማይገባውን ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የግል ተበዳይ የሆነው ሀ/ማርያም ገ/መስቀል የተባለ የግል ተበዳይ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ኛ ሙስና ወንጀል ችሎት በስልጣን ያለአግባብ መገልገል ወንጀል ክስ ቀርቦበት ጉዳዩን በማረሚያ ቤት ሆኖ መከታተል በነበረበት ጊዜ ተከሳሹ በታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም ተበዳይ ወደ ሚገኝበት የፌደራል ማረሚያ ቤት በመሄድ “እኔ በስራዬ ዳኛ ነኝ የአንተን ጉዳይ እያዩ የሚገኙትን 3 ዳኛዎች መቀሌ ዩኒቨርሲቲ አብሬያቸው ስለተማርኩኝ አውቃቸዋለሁኝ” በማለት ማግባባቱ በክሱ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም “ከዳኞቹ ጋር ተነጋግሬ በነፃ እንዲለቁህ አደርጋለሁ” በማለት የግል ተበዳዩን ካናገረው በኋላ በድጋሚ ወደ ተበዳይ በመሄድ “ዳኞቹን አናግሬ በብይን በነፃ እንድትለቀቅ 1ሚሊየን 200 ሺህ ብር ጠይቀውኛል በማለትና “እኔ ተደራድሬ 600 ሺህ ብር አስደርጋለሁ” ማለት ማግባባቱም በክሱ ተመላክቷል።
ከዚህም በኋላ ደግሞ በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም ላይ “ዳኞቹ አሁን በቅድሚያ 400 ሺህ ብር ካልተከፈለን ምንም አናደርግም ብለዋል” በአስቸኳይ ብር አምጣ በማለት አሳሳች ነገር በመናገር እና የተበዳይን የተሳሳተ ዕምነት በመጠቀም አታሎ 2ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ከሆነው የግል ተበዳይ ወንድም በሆነው ግለሰብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል በግንቦት 20 ቀን 2014 ዓ.ም 400 ሺህ ብር የተቀበለ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሶ በከባድ ማታለል የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶበታል።
ተከሳሹም ችሎት ቀርቦ ማንነቱን ካረጋገጠ በኋላ የቀረበበት ክስ ዝርዝር እንዲደርሰው ተደርጓል።
ፍርድ ቤቱም ተከሳሹ የክስ መቃወሚያ ካለው ለመጠባበቅ ለፊታችን ማክሰኞ የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ተቀጥሯል።
በታሪክ አዱኛ