Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ የአፍሪካን ሥርዓተ-ምግብ ለመለወጥ ሁሉም እንዲረባረብ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ የአፍሪካን ሥርዓተ-ምግብ ለመለወጥ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ጠየቁ፡፡

“አፍሪካ ራሷን በምግብ ትችላለች” በሚል መሪ ሐሳብ ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የውይይት መድረክ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ 90 በመቶ በአፍሪካ ያለው የግብርና ተግባር በተበጣጠሰ መንገድ የሚከናወን መሆኑን አንስተዋል፡፡

አርሶ አደሮችም በአየር ንብረት ለውጦች እየተፈተኑ ነው ብለዋል።

በምግብ አምራችነት ውስጥ ትልቅ ፈተና እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋምም በትጋት መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

አፍሪካ በምግብ እህል ራሷን እንድትችል ጊዜው አሁን በመሆኑ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል አበረታች ሥራዎችን እየሠራች መሆኗን ጠቁመው÷ለአብነትም የአረንጓዴ ዐሻራ ተግባራትን፣ የሀገር አቀፍ የስንዴ ልማት እና የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብሮችን ጠቅሰዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ፕሬዝዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ፣ የቱኒዚያ ጠቅላይ ሚኒስትር አሕመድ ሀሻኒ፣ የቻድ የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ሰክሰስ ማስራን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮችና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።

በምስክር ስናፍቅ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.