Fana: At a Speed of Life!

የወጣቱን አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል በፖሊሲ የተደገፈ ሪፎርም ማድረግ እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የወጣቱን እምቅ አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል መንግስታት በፖሊሲ አቅጣጫ የተደገፈ ሪፎርም ሊያደርጉ እንደሚገባ በአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ወጣቶች ልዩ መልዕክተኛ ችዶ ምፔምፓ ተናገሩ፡፡

ከ37ተኛው የአፍሪካ ሕብረት መደበኛ ጉባዔ ጎን ለጎን ልዩ መልዕክተኛዋ በሰጡት ማብራሪያ÷ አፍሪካ ያልተነካ እምቅ አቅም ባላቸው የወጣቶች ኃይል የተሞላች መሆኗን አንስተዋል።

ይህ የወጣት ኃይል የአኅጉሪቱን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ በአዲስ እይታ የማሸጋገር አቅም እንዳለውም ገልፀዋል።

በመሆኑም በተለይ በአህጉሪቱ የሚታየውን ሰፊ የወጣቶች ስራ አጥነት ለመቅረፍ ወጣቶችን ማስተማርና ማሰልጠን ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

የአኅጉሪቱ ወጣቶች በስራ ፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ እንዲሳተፉ ድጋፍና ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል ማታቸው ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የወጣቱን ሰፊ እምቅ አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል መንግስታት በፖሊሲ አቅጣጫ የተደገፈ ሪፎርም ሊያደርጉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ወጣቶችን በአካታች የልማትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ በሚጠበቀው ልክ በማሳተፍ በአኅጉሪቱ የሚጠበቀውን ለውጥ ማረጋገጥ ይቻላል ነው ያሉት፡፡

በአፍሪካ የተያዘውን የአጀንዳ 2063 ዕቅድ ለማሳካት 62 በመቶ በላይ የሆኑት የአኅጉሪቱ ወጣቶች ሚና ሰፊ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.