በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት ሕዝቡን ማሳተፍ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው የበጀት ዓመት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚከናወኑ ዘርፈ-ብዙ የልማት ተግባራት በተቀናጀ አግባብ ሕብረተሰቡን በማሳተፍ እንዲከናወኑ የክልሉ ካቢኔ አቅጣጫ አስቀመጠ፡፡
ካቢኔው ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በበጀት ዓመቱ ከተረጂነት ለመላቀቅ ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ የሕብረተሰቡን ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ እንደሚባ ገልጿል፡፡
በዚህም በክልሉ በአጋር ድርጅቶች የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ ሊያደርጉ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ብሏል፡፡
ከተሞችን ፅዱ፣ ውብ እና ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ፣ የደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን ማስፈን፣ በጤና፣ ትምህርት፣ ግብርና፣ የቱሪዝም ሀብቶችን ማልማት፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት፣ የማዕድን ዘርፉን በልዩ ትኩረት በመምራት የወጣቶችን የስራ ዕድል ፈጠራ ማሳደግ እንደሚገባም ካቢኔው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
የገቢ አሰባሰብ ስራዎችን በተመለከተም አቅምን አሟጥጦ በአግባቡ በመሰብሰብ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ ነው የተገለጸው፡፡
በበጀት ዓመቱ በኢንቨስትመንት፣ በኢንዱስትሪ እና በአምራች ዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ወደ ስራ በማስገባት ከዘርፉ የሕዝቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሠራት እንዳለበትም ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የሌማት ትሩፋት፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ የመስኖ እና የአረንጓዴ ዐሻራ ስራዎች፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ መቀመጡን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡