Fana: At a Speed of Life!

በ22 የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች ላይ ርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና ብልሹ አሠራርን ለመቅረፍ በተከናወነ ሥራ በ22 አመራርና ሠራተኞች ላይ አሥተዳደራዊ ርምጃ መውሰዱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ርምጃው የተወሰደው ከደንበኞች የቀረቡ የብልሹ አሠራርና ሙስና ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ መሆኑን ተቋሙ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

በዚሁ መሠረት አስፈላጊው ማጣሪያ ተደርጎ ሦስቱ በጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እና 19ኙ ደግሞ በደመወዝ ቅጣት መቀጣታቸውን ነው ያስታወቀው፡፡

በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሰባት ወራት 50 ሚሊየን 222 ሺህ 987 ነጥብ 7 ብር የሚገመት የንብረት ስርቆት እና ውድመት ተፈጽሞብኛል ብሏል ተቋሙ፡፡

የተፈፀመው ስርቆትና ውድመትም የኃይል ስርቆት፣ የትራንስፎርመር ስርቆት፣ ቆጣሪ መነካካት፣ የኤሌክትሪክ መስመር ጉዳት፣ የመሰረተ ልማት ስርቆት፣ የተቋሙ ሠራተኞችን ሥራ እንዳይሠሩ ማወክና የኬብል ስርቆትን የሚያጠቃልል መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ 163 ወንጀሎች ተፈጽመው ክትትል እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ነው የተገለጸው፡፡

ከእነዚህ መካከል 11 የወንጀል ጉዳዮች ውሳኔ ማግኘታቸው እና በዚህም 13 ተከሳሾች ከሁለት ወር ቀላል እስራት እስከ 10 ዓመት ፅኑ እስራት እና እስከ 50 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ መቀጣታቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የፍጆታ ክፍያ ለማይከፍሉ ለ368 ደንበኞች ማስጠንቀቂያ በመስጠት 127 ሚሊየን 840 ሺህ 606 ነጥብ 52 ብር ለተቋሙ ገቢ ማድረግ መቻሉ ተጠቁሟል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.