እንደ ኢሬቻ ያሉ የይቅርታና ምስጋና እሴቶች ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ጉልህ ድርሻ አላቸው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እንደ ኢሬቻ ያሉ የይቅርታ እና ምስጋና እሴቶች ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ጉልህ ድርሻ አላቸው አለ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡
አገልግሎቱ የ2018 የኢሬቻ በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ኢሬቻ ኢትዮጵያ ለዓለም የምታበረክተው ድንቅ እሴቷ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ለዓለም አበርክታለች፡፡
እሴታቸውን ጠብቀው ለዘመናት በሕዝብ እየተከበሩ የዘለቁ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላትንና ትውፊቶቻቸውን በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርት እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የሰው ልጆች ሁሉ ሀብት ተብለው እንዲመዘገቡም አድርጋለች፡፡ ለምዝገባ በሂደት ላይ የሚገኙ በርካታ እሴቶች ባለቤትም ነች፡፡
ኢሬቻ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በየዓመቱ የሚከበር የይቅርታ እና የምስጋና በዓል ነው፡፡ በዓሉ በዋናነት ክረምት በሰላም አልፎ አዲስ ዘመን መበሰሩን አስመልክቶ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ነው፡፡
ምስጋናው ደግሞ ይቅርታን ያስቀድማል፤ የተጣላ ይቅር ተባብሎ በአንድ ቦታ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት ነውና፡፡ ይህ ድንቅ የኢትዮጵያ እሴት የዓለም ሀብት እንዲሆን ኢትዮጵያ ለዘመናት ጠብቃዋለች፤ ትጠብቀዋለችም፡፡
የሚጠበቀው ደግሞ በዓሉን ትውፊቱን፣ እሴቱን፣ አሳታፊነቱን ጠብቆ በማክበር እና በማስተዋወቅ ነው፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ እና መላው ኢትዮጵያውያን የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል ምስጋና የሚያቀርቡት በጋራ ድላቸው ያሳኩትን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የደስታ ስሜት እያጣጣሙ ነው፡፡
በይቅርታ መሻገር፤ በጋራ ድል ማድረግ፤ በጋራ ማመስገን የኢትዮጵያውያን መገለጫ ነውና፤ እንደ ኢሬቻ ያሉ የይቅርታ እና ምስጋና እሴቶች ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ጉልህ ድርሻ አላቸው፡፡