ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ አለ ጤና ሚኒስቴር።
የዓለም የልብ ቀን “አንድም የልብ ምት አታምልጠን” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።
በእለቱም የኢትዮጵያ የልብ ማህበር አባላት፣ የህክምና ባለሙያዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ቀኑን ምክንያት በማድረግ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና የእግር ጉዞ አካሒደዋል።
ጤና ሚኒስቴርን በመወከል የተገኙት አቶ ሌሊሳ አማኑኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በአሁኑ ወቅት በማሕበረሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ካሉ ችግሮች ዋነኞቹ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ናቸው።
በዚሁ ሳቢያም መንግስት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል የሚያስችል የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የተጠናከሩ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ለአብነትም የባለሙያዎችን አቅም ማጠናከር፣ መድሃኒቶችን ከውጭ በማስገባት እና የልብ ቀዶ ጥገናዎች በዘመቻ እንዲካሔዱ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
መንግስት በሽታውን ለመከላከል ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ዜጎች አመጋገባቸውን በማስተካከልና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ራሳቸውን የመጠበቅ ባሕል ሊያጎለብቱ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የልብ ማኅበር ፕሬዚደንት እንዳለ ገብሬ በበኩላቸው÷ ማህበሩ የዓለም አቀፉ የልብ ቀን ምክንያት በማድረግ የልብ ሕክምናዎችን ከመስጠት ባሻገር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ከልብ ህመም ጋር ተያይዞ ሕክምና ለማግኘት በርካታ ዜጎች ተራ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው÷ አገልግሎቱን ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በተለይ በት/ቤቶች የልብ ህመም ጋር ተያይዞ ሕክምና የሚፈልጉ ዜጎችን መረጃ የመለየት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡