Fana: At a Speed of Life!

ጥራት የሌለው ትምህርት መዘዙ በክፍል ብቻ የሚቀር አይደለም – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ሚኒስትር እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ጥራት የሌለው ትምህርት መዘዙ በክፍል ብቻ የሚቀር አይደለም አሉ።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ76ኛ ዙር ያስተማራቸውን 6 ሺህ 417 ተማሪዎች አስመርቋል።

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ አንድን ትውልድ በዕወቀት ቀርጾ አለማውጣት ለተቋማዊ ድክመት ምክንያት ነው ብለዋል።

ጥራት የሌለው ትምህርት መዘዙ በክፍል ብቻ የሚቀር እንዳልሆነም አስገንዝበዋል።

ተቋማት በግልጽነት እና በታማኝነት የህዝብ አገልጋይ ከመሆን ይልቅ ለብልሹ አሰራር የሚጋለጡት በዕውቀት የበለጸገ ትውልድ ማፍራት ባለማቻሉ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ይህንን ችግር ለመፍታት የተሻለ ስኬት ካስመዘገቡ ሀገራት ተሞክሮ በመቅሰም ወደ ስራ መገባቱን ገልጸው፤ በብቃት ላይ የተመሰረተ የሀገር በቀል ዕውቀት እና በግብረገብ መርህ የተቃኘ የትምህርት ስርዓት ተዘጋጅቷል ብለዋል።

በሌላ በኩል ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም አንስተዋል።

በተለይም ከዚህ ቀደም በገጠር አካባቢዎች መሰል ስራዎችን በመከወን ፍትሃዊ የትምህርት ተደራሽነትን በጥራት ለመከወን እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከክልሎች የተውጣጡ ተማሪዎች የሚማሩባቸው የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን የማስፋት ስራ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ሰባት አስርት ዓመታት ከ300 ሺህ በላይ ምሩቃንን ማፍራቱን ገልጸዋል።

የራስ ገዝ የመሆን ሂደቱን ያጠናቀቀው ዩኒቨርሲቲው የመውጫ ፈተናን በብቃት የሚያልፍ ብቁ ተማሪ መፍጠሩን አንስተዋል።

ተመራቂዎች ለሀገር የመፍትሄ አካል እንድትሆኑ ኃላፊነት ተጥሎባችኋል ሲሉም አሳስበዋል።

በይስማው አደራው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.