ፍትሕ ሚኒስቴር አገራዊ ጥሪውን ተከትሎ ለመጡ ዳያስፖራዎች በሕግ ነክ ጉዳዮች የሚያማክር ዴስክ ማቋቋሙን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍትሕ ሚኒስቴር አገራዊ ጥሪውን ተከትሎ ወደ አገራቸው ለመጡ ዳያስፖራዎች በኢንቨስትመንትና በበጎ አድራጎት ሥራዎች ለመሳተፍ የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ በሕግ ነክ ጉዳዮች የሚያማክር ዴስክ ማቋቋሙን አስታወቀ።
በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግስት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደው፥ የዳያስፖራው ማህበረሰብ በኢትዮጵያ የፈተና ወቅት ለሀገራቸው በመቆም የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር መንግስትና ሕዝብ የወሰደውን እርምጃና እንቅስቃሴ በመደገፍ በመላው ዓለም ድምጽ በመሆን እና እውነታውን ለአለም በመግለጽ ላሳዩት የሀገር ፍቅርና ላደረጉት ተጋድሎ እንዲሁም ላስገኙት ውጤትና ለፈጠሩት በጎ ተፅዕኖ ተቋማቸው ያለውን ታላቅ አክብሮትና አድናቆት ገልጸዋል።
አያይዘውም በአገር ቤት በሚኖራቸው ቆይታ ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆንና የመጡበትን ዓላማ እንዲያሳኩ የፍትሕ ሚኒስቴር አገልግሎት እና ድጋፍ እንደማይለያቸው አረጋግጠዋል፡፡
ለዚህም የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በኢንቨስትመንት እና በበጎ አድራጎት (ግብረ ሰናይ) ሥራዎች ለመሳተፍ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከኢንስትመንት አንጻር ያሏቸውን መብቶችና ጥቅሞች፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እኩል ኢንቨስት ስለሚያደርጉባቸው የሥራ ዘርፎች፣ ከመንግስት ጋር በቅንጅት ኢንቨስት ስለሚያደርጉባቸው ዘርፎች፣ ከአገር ውስጥ ወይም ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በቅንጅት ስለሚያከናውኗቸው የኢንቨስትመንት ሥራዎችና የሕግ አግባብ፤ ከንግድ ሥራ ጋር በተያያዘ ከአዲሱ የንግድ ሕግ አንጻር ሊገነዘቧቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ የሕግ ምክርና ድጋፍ የሚሰጥ ዴስክ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውስጥ መቋቋሙን ሚኒስቴር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡
ከኢንስትመንት ጉዳዮች በተጨማሪ የዳያስፖራ አባላት በበጎ አድርጎት ሥራዎች ስለሚሳተፉበት፣ አጠቃላይ በሕግ ስለተከለከሉ እንዲሁም ዲያስፖራው በቆይታው ጥንቃቄ ሊያደርግባቸው የሚገቡ ጉዳዮችና ደህንነታቸውንና መብታቸውን በማስከበር ላይ ፍትሕ ሚኒስቴር አበክሮ እንደሚሰራ አስረድተዋል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ በመያዝ በአካል ወይም በወኪላቸው አማካኝነት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ካዛንችስ (ባምቢስ) አካባቢ በሚገኘው የፍትሕ ሚኒስቴር ዋናው መ/ቤት 4ኛ ፎቅ የፍትሃብሔር ፍትሕ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ጄነራል የሥራ ክፍል በመቅረብ የሕግ ምክርና ድጋፍ አገልግሎቱን ማግኘት እንዲሁም ተጨማሪ መረጃዎችን የስልክ ቁጥር +251111562325 በመጠቀም ማግኘት የሚችሉ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!