Fana: At a Speed of Life!

የጭነት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፋማነት መቀጠሉን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የጭነት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፋማነት መቀጠሉን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ገለጹ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ፥ በዱባይ በተዘጋጀው የበይነ-መረብ ውይይት ላይ እንደተናገሩት፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አበረታች ትርፋማ መሆኑን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ ትርፋማ ሊሆን የቻለው ከተለያዩ ሀገራት የጭነት አገልግሎት ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
አየር መንገዱ ባለፉት ሁለት አመታት በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የኦንላይን ሽያጭ እና በአቅርቦት ገበያ ላይ የተፈጠረው መዛነፍ ያመጣው የጭነት አገልግሎት ፍላጎት መጨመርን ዓየር መንገዱ እንደተጠቀመበት ነው ያመለከቱት።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት አገልግሎት ጠንካራ የሚባል ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፥ አገልግሎቱ በኩባንያው ውስጥ ዋነኛ የገቢ ምንጭ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ወረርሽኙን ተከትሎ በተፈጠረው የተቀዛቀዘ የተጓዦች አገልግሎት ተቋሙ ጉልህ ጉዳት እንዳላስተናገደ እና ያለምንም የገንዘብ ድጋፍ ሥራውን ቀጥሎ ከወረርሽኙ በፊት የነበረውን አፈፃፀም 70 በመቶ አሁን ላይ መፈፀሙን ነው ያመለከቱት።
የመንገደኞች የጉዞ ፍላጎት በየዓመቱ እየተሻሻለ ሲሆን፥ በፈረንጆቹ 2022 አየር መንገዱ ሊያሳፍር የሚችለው የመንገደኞች ቁጥር ከ2021 የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ሀገራት ለኮሮና ቫይረስ ወረሽኝ የሰጡት የተበጣጠሰ እና ያልተቀናጀ ምላሽን የተቹት ዋና ስራ አስፈፃሚው፥ ይህ እርምጃቸው የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪውን ክፉኛ እንደጎዳው ነው ያመለከቱት።
በቅርቡ የመካከለኛው ምስራቅ የጉዞ ማዕከል የሆነቸው ዱባይ ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች 13 የአፍሪካ ሀገራትን የሚመጡ ሰዎች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ ወይም በዚያ እንዳያልፉ ማገዷን አንስተዋል።
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ3 እስከ 4 ሣምንት ለሚሆን ጊዜ ወደ ዱባይ ተሳፋሪ ማጓጓዝ እንዳልቻለ በመጥቀስ፥ እርምጃው ማንንም እንደማይጠቅም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.