የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ለዳያስፖራዎችና አልሚ ባለሃብቶች 500 ሄክታር መሬት ማዘጋጀቱን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በደብረ ብርሃን ከተማ መዋዕለ ንዋያቸውን አፍስሰው ለሚያለሙ ዳያስፖራዎችና አልሚ ባለሃብቶች 500 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብርሃን ገብረ ህይወት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት፥ የሀገር ጥሪን ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት የገቡ ዳያስፖራዎች እና ልማታዊ ባለሃብቶች ኢንቨስት የሚያደርጉበት 500 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል።
እስካሁን 10 ዳያስፖራዎች የፕሮጀክት ሃሳብ የያዘ ጥያቄ አቅርበዋል ያሉት ሃላፊው፥ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
በከተማዋ በኢንቨስትመንት ዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ዳያስፖራዎችና ባለሃብቶች በማኑፋክቸሪንግ፣ በሆቴል በቱሪዝም፣በከተማ ግብርና እና በማህበራዊ ዘርፎች እንዲሰማሩ በቂ ዝግጅት መደረጉም ተገልጿል።
ከ60 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 330 ኢንዱስትሪዎች ያሏት ደብረ ብርሃን ከተማ፥ 40 ኢንዱስትሪዎቿ ማምረትየጀመሩ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ በግንባታ እና በቅድመ ግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል።
በዚህም እስካሁን ከ20 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል የፈጠሩ ሲሆን፥ግንባታቸው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከ70 ሺህ በላይ ስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል።
በ2014 በጀት ዓመት በደብረ ብርሃን ከተማ የሚያለሙ 350 ባለሃብቶችን ለመሳብ እቅድ ተይዞ ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን 120 ባለሃብቶች በዘርፉ ተሰማርተዋል።
በሰላም አሰፋ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን