ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች እና የሰላም እናቶች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መከሩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች እና የሰላም እናቶች በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት ካደረጉ በኋላ ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።
በአቋም መግለጫቸው የሀገር ሽማግሌዎች አባ ገዳዎችእና የሰላም እናቶች ጦርነት በተካሄደባቸው የሀገራችን ክልሎች በደረሰው ሞት፣ ውድመት እና መፈናቀል የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እንገልጻለን ብለዋል።
ሁሉም አካላት በጦርነቱ የተጎዱ ክልሎችን መልሶ ለመገንባት እና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ እናደርጋለን ነው ያሉት ።
በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የተፈጠረውን መቃቃር ለመፍታት የአገራዊ ምክክር መድረኩ ጉልህ ድርሻ መጫወት እንዳለበት ጥሪ እናቀርባለንም ነው ያሉት።
መንግስት በተደጋጋሚ እስረኞችን በመፍታት አገራችን ሰላማዊ እንድትሆን ያደረግነውን ጥሪ ተቀብሎ በእስር ላይ የነበሩ የተወሰኑ ሰዎችን ክስ ማቋረጡ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በማሳየቱ እናደንቃለን በማለት አሁንም በጀመረው አኳኋን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ክልሎችም ይህንኑ መንገድ እንዲከተሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን ብለዋል።
በቅርቡ ከእስር የተፈቱትም በበኩላቸው፥ የተጀመረው የሰላም መንገድ እውን እንዲሆን የራሳቸውን በጎ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ እናደርጋለን ብለዋል።
እኛ የሃገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች እና የሰላም እናቶች በአገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ታጥቀው ጫካ ያሉ ወገኖችም ወደ ሰላማዊ መድረክ ተመልሰው ግጭቶችን በምክክር እንዲፈቱ ጥሪ እናደርጋለንም ነው ያሉት ።
መንግስትም በበኩሉ ይህንኑ ጥሪ ተቀብሎ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች እንጠይቃለን ብለዋል።
ከላይ የተዘረዘሩ የሰላም ጠረቶች እና ውጥኖች ተግባራዊ እንዲሆኑ እና ዘላቂነት እንዲኖራቸው 11 አባላት ያሉበት አገር አቀፍ የሰላም ቡድን ማቋቋማቸውን ይፋ አድርገዋል።
በይስማው አደራው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!


0
People reached
0
Engagements
Boost post
Like
Comment
Share