የድሬደዋ አስተዳደር አመራሮች በከተማዋ የሚገኙ ተቋማትንና የልማት ፕሮጀክቶችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር አመራሮች በከተማዋ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችን እና የምሥራቅ አየር ምድብን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ከድር ጁሀርን ጨምሮ የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ እንዲሁም ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህን እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በድሬዳዋ ደረቅ ወደብ ሬዳዋ ሞተርስ የምሥራቅ አየር ምድብ እና የድሬደዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
ጉብኝቱ አመራሩ እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች ያሉበትን ደረጃ በመመልከት ለቀጣይ የልማት ጉዞ በየተሰማራበት መስክ የድርሻውን እንዲወጣ ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ስለመሆኑ ተመላክቷል፡፡
ድሬዳዋ አሁን ያላትን የልማት አቅም ሙሉ ለሙሉ በመጠቀም ለዜጎች በቂ የስራ እድል በመፍጠር በስራ ላይ ያሉትን ኢንዱስትሪዎች አቅም ማጎልበትና ተጨማሪ ኢንዱስትሪዎች በከተማዋ ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ በጉብኝቱ ተገልጿል፡፡
በዚሁ ጊዜ ከንቲባ ከድር ጁሀር እንደገለጹት÷ በተለይ አመራሩ የተጣለበትን ህዝባዊ አደራ በአግባቡ እንዲወጣ እና ወደ ከተማዋ ለሚመጡ ኢንዱስትሪዎች ምቹ እድል እንዲያመቻች መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የምሥራቁ ብሎም የሀገር የሰላም ዋስትና የሆነውን የምስራቅ አየር ምድብ እንዲሁም በፈጣን የሪፎርም ሂደት ውስጥ ያለውን የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በመጎብኘት አመራሩ ልምዶችን በመቅሰም በየዘርፉ ውጤታማ ስራ እንዲሰራ ጥሪ መቅረቡን ከድሬዳዋ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡