Fana: At a Speed of Life!

የፌደራል ፖሊስ ልዩ የክትትል አባላት ነን በማለት ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በመጠቀም የዝርፊያ ወንጀል ሲፈፅሙ የተገኙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 1 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ልዩ የክትትል አባላት ነን በማለት ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያና ሐሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም ተደራጅተው የዝርፊያ ወንጀል ሲፈፅሙ የተገኙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ  ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ÷ ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በመታጠቅ እና ሐሰተኛ የፖሊስ መታወቂያ በመያዝ ፖሊስ መስለው ወንጀል የሚፈፅሙ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

ለአብነት የሚጠቀሙባቸው ስሞች ባይሳ ገመቹ እና መርጋ  ጋሩማ በሚሉና  ትክክለኛ ባልሆኑ መታወቂያዎች አዲስ ከተማ ክ/ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው መርካቶ ይርጋ ኃይሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የወንጀል ድርጊት ሲፈፅሙ ፖሊስ  ደርሶባቸው በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል ግለሰቦቹ ህብረተሰቡን ለማደናገር በቀድሞ የፌደራል ፖሊስ ሠራዊት ሬንጀር የደንብ ልብስ ለብሰው በተነሱት ፎቶግራፎች የተዘጋጀ ሐሰተኛ መታወቂያ በመጠቀምና እንዲያሳዩ ሲጠየቁ እንዳይታወቅባቸው በርቀት በማሳየትና በያዙት የጦር መሳሪያ በማስፈራራት ተጨማሪ የወንጀል ተግባር ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ፖሊስ  የደረሰባቸው መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ከዚህ ባለፈም  ተጠርጣሪዎቹ የወንጀል ድርጊቱን የሚፈጽሙት የፌደራል ፖሊስ ልዩ ክትትል አባላት ነን በማለት በተለያዩ የንግድ ቦታዎች ተሰማርተው በነጋዴው ማህበረሰብ ላይ ጫና በመፍጠር ለዚህ እኩይ ዓላማ ማስፈፀሚያ በሚገለገሉበት ህገወጥ  መታወቂያና የጦር መሣሪያ በማስፈራራት የተለያዩ ገንዘቦችንና ሞባይሎችን ሰርቀው ሲሰወሩ እንደነበር ተረጋግጧል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የሚጠቀሙበት መታወቂያ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ  ከሚገለገልበት መታወቂያ ጋር በእጅጉ የሚለይ ሲሆን÷ ይዘውት የተገኘው የጦር መሣሪያና ህገ-ወጥ ገንዘብ በተመለከተ ሙሉ መረጃ ለማግኘት ፖሊስ ምርመራውን አጠናክሮ መቀጠሉም ተገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ይህንን ድርጊት የሚፈፅሙት በተደራጀ መልኩ መሆኑንና ግብረአበሮች እንዳሏቸው አመላካች መረጃ በመገኘቱ ምርመራው ተጠናክሮ መቀጠሉም ተጠቁሟል፡፡

ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላካልና የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፤ ከአዲስ አበባ ፖሊስ እና ከሌሎች የፀጥታና ደህንነት አካላት ጋር በመሆን ጥብቅ ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ እንደሚቀጥል  ነው ያረጋገጠው፡፡

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አደረጃጀት ውስጥ ልዩ የክትትል ፖሊስ የሚል ስያሜ አለመኖሩን ህብረተሰቡ እንዲያውቅና ከፀጥታ አከላት ጋር ሆኖ ከነዚህ ዓይነቱ አጭበርባሪዎች ራሱን እንዲከላከል ፖሊስ አሳስቧል።

ህዝቡ ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ሲያጋጥመው ትክክለኛውን የፖሊስ የደንብ ልብስና መታወቂያ መሆኑን ማረጋገጥ፤ የሚያጠራጥር ሁኔታ ሲኖር በአፋጣኝ  በስልክ ቁጥሮች +251115-52-63-03፣ +251115-52-40-77፣  +251115-54-36-78 እና  +251115-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች በመጠቀም ጥቆማ በመስጠት ወይም በአካባቢው ለሚገኝ የፀጥታ ኃይል መረጃውን በአካል በማድረስ የተለመደ ድጋፍና ትብብሩን እንዲያደርግ  ጥሪ ቀርቧል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.