ብሔራዊ የንግድ ፖርታል ኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የንግድ ስራን ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችል ብሔራዊ የንግድ ፖርታል ኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ይፋ ሆነ።
አገልግሎቱ ዜጎች ኢንተርኔትን ተጠቅመው የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ አገልግሎትን፣ የንግድ ስራ አጀማመርና ፈቃድ አወጣጥ ሂደትን እንዲሁም የመረጃ አሰጣጥ ስራን በቀጥታ የአንድ መስኮት አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጀ መሆኑን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
ብሔራዊ የንግድ ፖርታል የኤሌክትሮኒክ አገልግሎቱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽንና ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን፣ ከንግድ እና ገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
በፕሮግራሙ ላይ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አህመዲን ሙሀመድ፥ የኤሌክትሮኒክ አገልግሎቱ መንግስት ከያዘው የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ውስጥ የንግድ ስራውን የማሳለጥ እና አገልግሎቱን ዘመናዊ ቀልጣፋና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ከሚሰሩ ስራዎች ውስጥ አንዱ ነው ብለዋል።
የኢ- ገቨርን ፕላት ፎርሙ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን እና የመሬት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ቢሮዎች የተዘጋጀ ሲሆን፥ በውስጡ ብሄራዊ ቢዝነስ ፖርታል፣ የኢ-ሰርቪስ ፕላት ፎርም እና ክፍት የመረጃ ልውውጥ ስርአትን ይዟል።
አሰራሩ ኢትዮጵያ ወደ ዲጅታል ትራንስፎርሜሽን የምታደርገውን ጉዞ ከማሳካት በተጨማሪ የዘርፉን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በማሳደግ የሚባክን ወጪ፣ ጊዜ እና ጉልበት በመቀነስ የሀገሪቷን ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ያዘምናል።
በተጨማሪም በፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የሚሰጥ ለጭነት ተሽከርካሪ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች የድንበር ተሻጋሪ ፈቃድ መስጠት፣ በፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የሚሰጥ የተሽከርካሪ ወደ ሃገር ውስጥ ማስገቢያ ፈቃድ መስጠት፣ የወሳኝ ኩነትና ዜግነት ምዝገባ፣ በኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የሚሰጥ የተመዘገቡ የአካውንቲንግና ኦዲቲንግ ድርጅቶች እድሳት መስጠት እና ሌሎች አገልግሎቶችም ይገኙበታል።
ቢዝነስ ፖርታሉ በተዘጋጀለት ድህረ ገጽ (www.eservices.gov.et/business/hom) አማካኝነት በአማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች እንዲሰራ ሆኖ የተዘጋጀ ሲሆን በቀጣይ በመላ ሀገሪቱ በሌሎች ቋንቋዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል ተብሏል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision