Fana: At a Speed of Life!

የመጀመሪያው የቻይና – አፍሪካ ቀንድ አገራት የሰላም ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጀመሪያው የቻይና – አፍሪካ ቀንድ አገራት የሰላም ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ኮንፈረንስ በአፍሪካ ቀንድ እና በቻይና መካከል ያለውን ትብብር መሰረት ያደረገ በሰላምና ፀጥታ፣ በልማት እንዲሁም በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ምክክር ይደረጋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ፥ በበርካታ ችግሮች የተወጠረው የአፍሪካ ቀንድ ሰላማዊ እና የተረጋጋ እንዲሆን ቻይና ለምታደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፤ በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ብለዋል።

አክለውም 300 ሚሊየን ህዝብ የያዘው የአፍሪካ ቀንድ ለዘመናት ግጭት፣ ሞት፣ መፈናቀል እና ስደት ከተፈጥሮ አደጋዎች ጋር ተዳምሮ እየፈተኑት እንደሚገኝ አንስተዋል።

በዚህም ህዝቡን ከድህነት ለማላቀቅ ጠንካራ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመንደፍ የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት መስራት አለብን ሲሉ ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ የቀጠናውን ህዝብ የእርስ በርስ ግንኙነት ማሳደግ ይኖርብናልም ነው ያሉት።

የቻይና በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዥው ቢንግ በበኩላቸው ፥ በኮቪድ 19፣ በድርቅ፣ በጦርነት እና በስደት የሚፈተነውን የአፍሪካ ቀንድ ለመደገፍ ቻይና በርካታ ስራዎችን እየሰራች እንደምትገኝ ጠቅሰው፥ ቻይና አሁንም ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አመላክተዋል።
በተለይም በቀጠናው ሰላም እና ፀጥታ እንዲሰፍን በምግብ ፣ በቴክኖሎጂ ትብብር፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ እና ሽብርተኝነትን ለመከላከል ከሃገራቱ ጋር እንሰራለን ብለዋል።

እስካሁን ለአገራቱ ቻይና ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነች ሲሆን ፥ በጥናት እና ምርምር የታገዘ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በራሳቸው የኢኮኖሚ አቅም እንዲያሳድጉ የሰው ሃይል በሙያ እና ክህሎት እንዲዳብር የተለያዩ ስልጠናዎችን እየሰጡ እንደሚገኙም ልዩ መልዕክተኛው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የህዝብ ለህዝብ ትስስር በአገራቱ መካከል እንዲያድግ በመሰረተ ልማት ግንባታ ሌሎች ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በምክክሩ የጂቡቲ፣ ኬኒያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና የዑጋንዳ ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።

በምንይችል አዘዘው

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.