ሳዑዲ የአውሮፓ ሀገራትን ጨምሮ በ50 ሀገራት ላይ የጉዞ እገዳ ጣለች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሳዑዲ ዓረቢያ ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ሀገራትን ጨምሮ 50 በሚደርሱ ሀገራት ላይ የጉዞ እገዳ መጣሏን አስታውቃለች።
የጉዞ እገዳው በአሁኑ ወቅት በሳዑዲ ዓረቢያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የተጣለ መሆኑ ተገልጿል።
በውሳኔው መሰረት የአውሮፓ ሀገራትን ጨምሮ 50 ከሚደርሱ ሀገራት ወደ ሀገሪቱ ብሎም ከሀገሪቱ ወደ ሀገራቱ የሚደረግ ማንኛውም በረራ በጊዜያዊነት ታግዷል።
ከአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምር ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን የጉዞ እገዳ ተጥሎባቸዋል።
በጉዞ እገዳው 28 የአውሮፓ እና ስድስት የእስያ ሀገራትም ተካተዋል ነው የተባለው።
በአሁኑ ወቅት በሳዑዲ ዓረቢያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 45 መድረሱን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ምንጭ ፦www.arabnews.jp/en