የዐቃቤያነ ሕግን የሥራ አፈጻጸም የሚመዝን አዲስ ሥርዓት ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትሕ ሚኒስቴር የዐቃቤያነ ሕግን የሥራ አፈጻጸም የሚመዝን አዲስ ሥርዓት አጥንቶ ሥራ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
በሠራተኞች መካከል ውድድርን በማበረታታት የተገልጋይን እርካታ ለመጨመር፣ ወጥ እና ዘመናዊ የባለሙያዎች የሥራ አፈጻጸም መመዘኛ ሥርዓት ሊኖር ይገባል ሲል ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
የምዘና ስርዓቱ ያለበት ክፍተት ቢስተካከል ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚችል ባለሙያን ለመፍጠር እንደሚያስችል ታምኖበት አዲስ የዐቃቤያነ ሕግ አፈጻጸም ምዘና ሥርዓት መመሪያ ቁጥር 32/2014 ወጥቶ በስራ ላይ መዋሉ ተጠቅሷል፡፡
በመመሪያው የተደነገገው የመመዘኛ ስርዓት ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አስገዳጅነት ያለውና እያንዳንዱን ተግባራት፣ ክብደት እና ውስብስብነት ከግምት ያስገባ ከመሆኑም በላይ አፈጻጸሞች ከውጤት ባሻገር ቅልጥፍናን፣ ጥራት እና የሥነ-ምግባር ሁኔታን ከግምት ያስገባ መሆኑ ለየት ያደርገዋል ሲሉ የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ እና ፕሮጀክት መከታተያ ዳይሬክተር አቶ ኖህ ታከለ ገልጸዋል፡፡
በምዘና ስርዓቱ ዐቃቤያነ ሕግ ብቻ ሳይሆኑ የስራ ክፍል ኃላፊዎችም ጭምር እንደሚመዘኑ ጠቅሰው፥ በተለይም በአመራር ክሕሎት የሙያ ብቃት እንዲሁም የስራ ውጤታማነት ከፍተኛ ነጥብ እንዲይዙ መደረጉ ኃላፊዎች በውድድር ስሜት በዕቅድ የያዙትን ተግባር በተሻለ ውጤት ማከናወን እንዲችሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ሥርዓቱ በምዘናው አነስተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ ፤ እንዲሁም የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡትን ደግሞ ለማመስገን እና ለማበረታታት ሌሎችም ከዚሁ ተሞክሮ በመውሰድ በተቋም ደረጃ ተቀራራቢ የአገልጋይነት ስሜት እንዲፈጠር የራሱ ሚና አለውም ተብሏል፡፡
በተቋሙ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሥር የሚገኙ የሥራ ክፍሎች ኃላፊዎች በተገኙበት የምዘና ስርዓቱን ይዘት እና አተገባበር በዐቃቤያነ ሕግ አስተዳደር ጉባዔ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይግረም ምንዳ አማካኝነት ቀርቦ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ ስርዓቱ ወደ ተግባር መግባቱ ይፋ ሆኗል መባሉን ከፍትሕ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡