የኢትዮጵያ እና የዜጎቿ የአሸናፊነት ምሥጢር ከአባቶቻችን የወረስነው አንድነት እና ቁርጠኝነት ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “የኢትዮጵያ እና የዜጎቿ የአሸናፊነት ምሥጢር ከአባቶቻችን የወረስነው አንድነት እና ቁርጠኝነት ነው” ሲሉ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የልዑካን ቡድን ያስመዘገበውን ድል አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ “የኢትዮጵያ እና የዜጎቿ የአሸናፊነት ምሥጢር ከአባቶቻችን የወረስነው አንድነት እና ቁርጠኝነት ነው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ የአሸናፊነትን ተምሳሌት ለዓለም ሕዝብ ላሳዩት የኢትዮጵያ አትሌቶች እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ለተለያዩ ሰው-ሰራሽ እና የተፈጥሮ ችግሮች ተጋልጣለች፤ ነገር ግን ዜጎቿ አንድም ጊዜ ለእነዚህ ችግሮች እጅ ሳይሰጡ በአንድነት እና በጀግንነት ድል እያስመዘገቡ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ሀገር ማስቀጠል ችለዋል” ነው ያሉት አቶ ሽመልስ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ዛሬም እንደ አባቶቻቸው በሁሉም የትግል ሜዳዎች ድል እያመስዘገቡ ለአገራቸው ያላቸውን ፍቅር እያሳዩ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ጀግኖች አትሌቶቻችን በዓለም ሻምፒዮና ላይ ድንቅ ድል በማስመዝገብ አኩርተውናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በአሜሪካ ኦሪገን ሲካሄድ በቆየው 18ኛውን የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከአፍሪካ ቀዳሚ፣ ከዓለም ደግሞ ከአሜሪካ በመቀጠል 2ኛ ደረጃን ይዛ በሻምፒዮናው ታሪክ ከፍተኛው ሜዳሊያ በማግኘት አጠናቃለች፡፡