የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላት የማጠቃለያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በወልዲያ ከተማ በሰሜን ወሎ ሲከበሩ የቆዩት የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላት የማጠቃለያ መርሐ ግብር በወልዲያ ሞሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታዲየም እየተካሄደ ነው፡፡
በዛሬው ቀን በሰሜን ወሎ አካባቢ ያሉትን በዓላት እንደ ክልል የማጠቃለያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ሲሆን በዚህ መርሐ ግብር የወልዲያ ከተማ ወደ ሪጂዮፖሊታን እንድትሸጋገር በመደረጓ የምስጋና ፕሮግራምም ተደርጓል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ፥ ከተሞች የሚገባቸውን የደረጃ እድገት እያገኙ ሲሄዱ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት መስጠት ይችላሉ ብለዋል።
የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች የሪጂዮፖሊታን ደረጃን ሲጠይቁ መቆታቸውን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህም ከረጅም ጊዜ በኋላ ጥያቄያቸው መመለሱን ገልጸዋል፡፡
ይህም ከተማዋ የልማት፣ ለኑሮ ምቹነት እና አገልግሎት በተቀላጠፈ መልኩ እንድትሰጥ ከማድረግ በተጨማሪ ወልዲያ የነበራትን የልማት፣ የመከባበር እና የእድገት ውብ ታሪክ ማስቀጠል እንደሚስፈልግ አስገንዝበዋል።
መንግስት በበኩሉ ከተማዋ የተጓደለባትን ዋና ዋና መሰረተ ልማቶች በቀጣይ ለማከናወን ትኩረት እንደሚሰጥም አረጋግጠዋል፡፡
አያይዘውም ወራሪውን ሀይል ለማንበርከክ ህዝቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ አንድነቱን ሊያጠናክር እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በታሪኩ ለገሰ