የኢትዮጵያን እምቅ የታዳሽ ኃይል ሀብት በማልማት ለሀገራዊ እድገትና ለቀጣናዊ ትስስር ማዋል ይገባል – ኢ/ር ክፍሌ ሆሮ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን እምቅ የታዳሽ ኃይል ሀብት በማልማት ለሀገራዊ እድገትና ለቀጣናዊ ትስስር ማዋል እንደሚገባ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ ገለጹ።
ኢንጂነር ክፍሌ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ የሚኖረውን ሀገራዊና ቀጣናዊ ፋይዳ ያብራሩ ሲሆን ፥ ግድቡ ከሀይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል በዓመት እስከ 1 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ገቢ እንደሚያስገኝ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከውሃ ብቻ እስከ 45 ሺህ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ማመንጨት የምትችል መሆኑን ጠቁመው ፥ የእንፋሎት፣ የፀሐይ እንዲሁም የነፋስ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል እምቅ ሃብት አላት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በሌሎችም የልማት መስኮች ለቀጣናዊ የልማት ትስስር ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑንም ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ በሀይድሮ ኤሌክትሪክ ሀይል ከፍተኛ እምቅ ሀብት በመያዝ ከአፍሪካ ሁለተኛዋ ሀገር ብትሆንም፤ ከውሃ ሀብቷ የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ መቆየቷን አንስተዋል።
በሂደትም በፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ በመመስረት በድንበር ተሻጋሪው የዓባይ ወንዝ ላይ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ በማካሄድ ከውሃ ሀብቷ የኃይል ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራች መሆኑን አስረድተዋል።
ግድቡ በሁለት ዓመት ተኩል እንዲጠናቀቅ እየሰራን ነው ያሉት ኢንጂነር ክፍሌ ፥ በአሁኑ ወቅት ሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ ግንባታው ሙሉ ቡሉ ሲጠናቀቅ እና 11 ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ሲጀምሩ ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 1 ቢሊየን ዶላር ዓመታዊ ገቢ እንደምታገኝ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ ያሏትን የውሃ ሀብትና ሌሎች የታዳሽ ኃይል እምቅ ሀብት በማልማት ለሀገራዊ እድገትና ለቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር መጠናከር እንደምትሰራም አብራርተዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!