ተመድ የዜጎችን ደህንነት የሚያረጋግጡ ልማትና የተቀናጀ ሥራ እንዲሰራ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማሪያም በኢትዮጵያ የተመድ ቡድን ከዕለት እርዳታ ባሻገር የዜጎችን ደህንነት የሚያረጋግጡ ልማትና የተቀናጀ ሥራ እንዲሰራ ጠየቁ፡፡
አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማሪያም የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ከኢትዮጵያ የተመድ ተቋማት ኃላፊዎችና ተወካዮች ጋር ትውውቅ አድርገዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነሮች እና አማካሪዎች የተገኙ ሲሆን ፥ የተመድ የኢትዮጵያ ቡድን ኃላፊ ካትሪን ሶዚ፣ የተመድ የሰብዓዊ ድርጅቶች ማስተባበሪያ ፣ የዓለም ጤና ድርጅት፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የህፃናት አድን ድርጅት፣ የሴቶች፣ የተመድ የደህንነትና ሴፍቲ፣ የዓለም ስደተኞች ተቋም፣ የዓለም የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የተመድ በኢትዮጵያ ቡድን ኃላፊ ካትሪን ሶዚ እንደገለፁት ፥ የኢትዮጵያ መንግስትና የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በሀገሪቱ የዕለት ድጋፍ ለሚፈልጉና በአስቸኳይ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማቅረብ ከመንግስት ጎን ሆነው ለሚሰሯቸው ስራዎች እየተደረገላቸው የሚገኘውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አድንቀዋል፡፡
በትግራይ መቀሌ ለሰብዓዊ ድጋፍ ስራዎች የተላከውን ነዳጅ መዘረፉን በማውገዝ ድርጊቱ አሳዛኝ መሆኑን አንስተዋል።
በተመድ ደረጃ ከፍተኛ አመራሮችና በዋናው መስሪያ ቤት ደረጃ ጉዳዩ እየታየና ለዚህም አስፈላጊው ምላሽ እንደሚሰጥበት ገልፀዋል፡፡
በማጠቃለያም ኮሚሽነሩ በኢትዮጵያ የተመድ ቡድን እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴና ድጋፍ በማድነቅ ከዕለት እርዳታ ባሻገር የዜጎችን ደህንነት የሚያረጋግጡ ልማትና የተቀናጀ ሥራ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡
የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ከልማት ስራዎች ጋር በማቀናጀት ጠንካራ ሥራዎችን ለማከናወን ተጨማሪ የሃብት ቋቶችን የማስፋት፣ የተቀናጀና የተናበበ ዕቅድና ሐብት የማቅረብ አካሄድ መከተል ይገባልም ብለዋል።
ከዚህ ባለፈም በትግራይ መቀሌ የተዘረፈውን 12 መኪና ነዳጅ የሚመለስበትን መንገድ በጥብቅ እንዲሰራና ድርጊቱም በሀገሪቱ የተመድ ቡድን ደረጃ በጥብቅ እንዲወገዝ አስፈላጊ ስራዎች እንዲሰሩም ነው የጠየቁት፡፡
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደማይለያቸው መናገራቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!