ሰላማዊ መንገድ እንዳይዘጋ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ህወሓትን ወደ ሰላም መንገድ እንዲያመጣው መንግስት አሳሰበ
የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም ያደረገው ጥረትና የከፈለው ዋጋ መኖሩን የጠቀሰው መግለጫው፥ መንግሥት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ውሳኔ ማሳለፉን ገልጿል፡፡
በውሳኔው መሠረት የተናጠል ተኩስ አቁም ማድረጉን፣ ለእርዳታ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች እና ቁሳቁሶች ላልተገባ ተግባር መዋላቸውን እያወቀ እንኳን÷ ለሕዝብ ሲባል ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ እንዲገባ ሁኔታዎችን አመቻችቷል ነው ያለው፡፡
የድርድር ዕቅዱን እና ተደራዳሪዎቹን ይፋ በማድረግ፥ በየትኛውም ጊዜ፣ ቦታ እና ጉዳይ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑንም መንግሥት አስታውቋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሁን በግልጽ እንደታየው ህወሓት ነዳጅ ዘራፊ ብቻ ሳይሆን ጠብ ጫሪ መሆኑንም አውቆ ማውገዝ እንዳለበት ነው የገለፀው፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “ሁለቱ ወገኖች” ከሚል ፍርደ ገምድል ጥሪ ተላቆ መንግሥት ወደያዘው የሰላም አማራጭ ህወሓት እንዲመጣ ግፊት እንዲያደርግ መንግሥት ጥሪ አቅርቧል፡፡
ይህ ካልሆነ እና ህወሓት ጥቃቱን የሚቀጥል ከሆነ መንግሥት በሕግ የተጣለበትን ግዴታ ለመወጣት ሲል ማንኛውንም እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን አስታውቋል፡፡