Fana: At a Speed of Life!

የሠላም ስምምነት በመፈረሙ ያሸነፈችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ናት- ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሠላም ስምምነት በመፈረሙ ያሸነፈችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ናት ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ የሠላም ስምምነት መፈረምን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት÷ በመንግሥትና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድ በቆየው የሠላም ድርድር የሠላም ስምምነት ሊፈረም መቻሉን አንስተዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱም ታላቅ ሀገር ለሆነችው ኢትዮጵያና ለሕዝቧ እጅግ መልካም ዜና ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በእጅጉ ተጎድተናል ፤ ብዙዎችን አጥተናል ፤ ይህ ታላቅ ሕዝብ ላይ የደረሰው የማይገባው ነው፤ መሆን የሌለበት ነው ፤ በዚህች ምድርየተፈጸመው ፤ የጦርነት በጎ ገጽታ የለውም ነው ያሉት በመልዕታቸው፡፡

የሠላም ስምምነት በመፈረሙ ያሸነፈችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ናት ያሉት ፕሬዚዳንቷ ÷ ስምምነትን መተግበር፣ ቁስል እንዲሽር ማድረግ፣ መልሶ መገንባት፣ የተጎዱትን ማቋቋም… ወዘተ ቀላል ተግባር አለመሆኑንም እገነዘባለሁ ብለዋል፡፡

ሀገራችን ከዚህ ሁሉ አገግማ ወደሚገባት የእድገት ደረጃ ማድረስ ይጠበቅብናል ፤ መተዛዘን፣ መተሳሰብ፣ መደማመጥ፣ መከባበርን ልንላበሰው ይገባል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይህንን የምናደርገው የዚህች ሀገር ሴቶችና ወንዶች በአንድነት ነው ፤ በተለይ ሴቶች የጦርነት ሰለባ ብቻ ሳይሆኑ ትክክለኛ ጥያቄ የሚያቀርቡ፣ የመፍትሄ ሃሳብ የሚያመነጩም መሆናቸውን በተደጋጋሚ አይተናል ብለዋል፡፡

የሠላም ፍለጋ አካል መሆን እንደሚችሉም አሳይተዋል ፤ የኢትዮጵያ ሴቶች በሠላምና ፀጥታ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

የሀገራችንን አንድነትና ሠላም ለማስከበር ሕይወታቸውን ላጡ፣ ለቆሰሉ የመከላከያ ሠራዊታችን አባላት፣ ለጸጥታ ኃይሎቻችንና ዜጎቻችን በእጅጉ ከሚገባቸው ከእኛ ምስጋና በላይ ታሪክ ገድላቸውን በከፍተኛ ደረጃ ይመዘግበዋል ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦባሳንጆ፣ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ሌሎች አካላት ላደረጉት ያላሰለሰ ጥረት አመስግነዋል፡፡

አንዳንዶቹ አሁን የጀመሩት ሳይሆን ውስብስብና አስቸጋሪ ሁኔታ ያልበገራቸው መሆናቸውንም ነው የጠቀሱት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.