ተቋርጦ የነበረው ዜጎችን ከሳዑዲ የመመለሱ ሒደት የፊታችን ሰኞ እንደሚጀመር ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 9 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ተቋርጦ የነረበው ዜጎችን ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ሂደት የፊታችን ሰኞ እንደሚጀመር የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ እንደገለጹት፥ በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ቀሪ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል፡፡
የብሄራዊ አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚቴ ተቋርጦ የቆየውን ከሳዑዲ ዜጎችን የመመለስ ሒደት ማስቀጠል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ ማስቀመጡንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ዜጎችን የመመለሱ ስራ ከፊታችን ሰኞ ሕዳር 12 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚቀጥል ነው የተገለጸው፡፡
በሒደቱም ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚሄዱ ወገኖችን የመደገፍ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራ አቅጣጫ መቀመጡን አቶ ደበበ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በሁሉም ምዕራፍ የሚተገበሩ ስራዎች በጋራ ዕቅድ በቅንጅትና በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እንዲተገበሩና በየወቅቱ የተደራጀ የአፈፃፀም ግምገማ እንዲደረግ ማሳሰቢያ መሰጠቱንም ጠቁመዋል፡፡
ከሳዑዲ ዓረቢያ የሚመለሱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምም የሚመለከታቸው አካላት በቅርበት እና በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ ቀርቧል፡፡
እስካሁን 70 ሺህ በላይ ዜጎችን ከሳዑዲ ዓረቢያ የተመለሱ ሲሆን፥አሁን ላይም 30 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወገኖች በሳዑዲ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡
በመላኩ ገድፍ